“ካራማራ ከትላንት እስከ ዛሬ በተሻገረው የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ቋሚ መገለጫ ነው” ልጅ ዳንኤል ጆቴ

40

አዲስ አበባ: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የካራማራ ድል 47ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል በኢትዮ-ኩባ የወዳጅነት አደባባይ እየተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ የቀድሞው አርበኞች የፖሊስ እና ጦር ሠራዊት አባላት፣ የኢትዮ-ኩባ ማኅበር አባላት፣ የኩባ ዲፕሎማቲክ አባላት እና ሌሎች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ የኩባ አምባሳደር ማሬን ስዋሬዝ አልቫሬዝ ይህ የሁለቱ ሀገራት ጀግኖች በጋራ ለሰላም የከፈሉት ዋጋ ነው ብለዋል። ይህ ቀን የካራማራ ድል ብቻ ሳይኾን የሁለቱ ሀገራት 50ኛ ዓመት ዲፕሎማሲያዊ ድል ጭምር ነው ብለዋል። ኩባ እና ኢትዮጵያ ከትላንት የጀመረ ዛሬን የቀጠለ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደፊትም በወንድማማችነት ይቀጥላል ብለዋል።

የጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ካራማራ ከትላንት እስከዛሬ በተሻገረው የኢትዮጵያውያን ጀግንነት ቋሚ መገለጫ ነው ብለዋል። ዛሬ የካራማራን ድል አከባበር ለየት የሚያደርገው የትናንቱ ፖሊስ ሠራዊት እና መከላከያ ሠራዊት ከዛሬ መከላከያ ሠራዊት ጋር በጋራ ኾነው የሚያከብሩት መኾኑ ነው። ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት ነው፣ ለእኛ ሁለቱም ልጆቻችን ናቸው ብለዋል።

ኩባ፣ ጀርመን፣ ሩሲያ እና የመን በዚህ ጦርነት በመሳተፍ ኢትዮጵያን ማገዛቸውን ያነሱት ልጅ ዳንኤል ዛሬም ኢትዮጵያውያን በአንድ በመቆም ጠላትን ማሳፈር ይኖርባቸዋል ብለዋል። የቀድሞው የኢትዮጵያ የጦር ኃይሎች እና ፖሊስ ሠራዊት ማኅበራት ኅብረት ሰብሳቢ ብርጋዴል ጀኔራል ውበቱ ፀጋዬ በበኩላቸው “ዚያድባሬ እጅግ ትልቅ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ 700 ኪሎሜትር በምሥራቅ፣ በደቡብ 300 ኪሎ ሜትር ጥቃት ሲሰነዝሩብን ምንም ዝግጅት አልነበረንም። ይሁንና ምንም አልነበረንም የሚል ከሽንፈት የማይታደግ በመኾኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያንን አሥተባብረን ማሸነፍ ችለናል” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ያላት ስትራቴጂክ አቀማመጥ በመኖሩ ምክንያት በርካታ ጦርነቶች ታልፈዋል ብለዋል። ይሁንና በወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ባደረጉት የእናት ሀገር ጥሪ በአጭር ጊዜ በታጠቅ ጦር ሰፈር ዝግጅት በማድረግ አስቸጋሪውን ጦርነት ተወጥተናል ብለዋል።

የካቲት 26/1970 ዓ.ም ጠዋት ጀግናው የኢትዮጵያ ሠራዊት የካራማራ ምሽግን ሰበረ፤ ድልም አደረ። ይህ ጀግና ሠራዊት ግን ተገቢውን ክብር እና እንክብካቤ አላገኘም ሲሉም ትችት አቅርበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየካራማራ ተጋድሎ!
Next articleየካራማራው አብሪ ኮከብ – ብርጋዴል ጄኔራል ለገሰ ተፈራ!