
ባሕር ዳር: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሆ ብየ እመጣለሁ ሆብየ በድል
ጥንትም ያባቴ ነው ጠላትን መግደል
ሆ ብዬ እመጣለሁ ልበ ሙሉ ጀግና ፍራት የሌለብን
እኔስ ለኢትዮጵያ ቃልኪዳን አለብኝ
ያያት የቅድመ አያት ወኔ ያልተለየኝ
ዛሬም ለኢትዮጵያ ታጋይ ተጋዳይ ነኝ
ጀግኖች በደማቸው ያቆዩትን ሀገር
ዛሬም በልጆቿ ለዘላለም ትኑር
ባያት በቅድመ አያት የኖረች ተከብራ
አልያት በቁሟ እምየ ተደፍራ፡፡
ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማንበርከክም ኾነ ርስቷን ለመንጠቅ አጋጣሚውን ሁሉ ተጠቅመው የተደጋገመ የወረራ ሙከራ ያደረጉ ሁሉ የልጆቿን ነበልባል ክንድ ቀምሰው ተመልሰዋል። ከእነዚህ ሀገራት መካከል ደግሞ የሶማሊያ ተስፋፊ መንግሥት ዚያድባሬ አንዱ ነው። ከቅኝ ግዛት ነፃነት ማግሥት ጀምሮ በሶማሊያ መንበረ ሥልጣኑን የተቆናጠጠው መንግሥት በጅቡቲ፣ በሰሜን ምሥራቅ ኬኒያ እና በኢትዮጵያ የሚገኙ የሶማሊኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን በሙሉ በማዋሃድ “ታላቋን ሶማሊያ” የመመስረት አንድ ፕሮጀክት ነደፈ።
የፕሮጀክቱን የመጀመሪያ ትኩረት ያደረገው ደግሞ ኦጋዴን ላይ ነበር። የዓለም አቀፍ ሕግጋትን በመጣስ በ1953 ዓ.ም እና በ1956 ዓ.ም ድንበር ተሻግሮ በኀይል በኦጋዴን በኩል ወረራ የፈጸመው የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ሠራዊት ክፉኛ ተመትቶ ተመለሰ። በኢትዮጵያ ሠራዊት የተመታው የሶማሊያ መንግሥት ሕልሙን ለማሳካት መልካም አጋጣሚ እስኪፈጠርለት ድረስ መጠባበቅን መረጠ።
በ1969 ዓ.ም የኢትዮጵያን መንግሥት በራሱ ውስጣዊ የሥልጣን ሽኩቻ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እንደ አሸን ተፈልፍለው የነበሩ ድርጅቶች በየአካቢው የትጥቅ ትግል መጀመራቸው፣ ለ25 ዓመታት ወታደራዊ እርዳታ ስትሰጥ የኖረችው አሜሪካ ከእርዳታ ተቀባይ ሀገሮች ዝርዝር ሀገሪቱን መሰረዟን ተከትሎ መንግሥት ችግር ውስጥ ወደቀ።
በ1961 ዓ.ም የፕሬዝዳንት አብዱ ራሺድ አሊ ሸርማርኬን መንግሥት መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ ሥልጣን ለያዘው የዚያድባሬ መንግሥት ደግሞ “የታላቋ ሶማሊያ”ን ሕልም እውን ለማድረግ የተመቻቸ ጊዜ ፈጠረለት ። እስከ አዋሽ ወንዝ ድረስ ያለውን መሬት ጭምር ለመጠቅለልም ቆርጦ ተነሳ።
ከየካቲት/1969 ዓ.ም ጀምሮ በዋርዴር፣ በቀብሪዳሐር፣ በዶገነቡር እና በጎዴ አራት ብርጌዶችን፣ በድሬድዋ ግንባሮች ደግሞ ሦስት ብርጌዶችን በማሰለፍ ወረራ ፈጸመ።
በምሥራቅ 700 ኪሎ ሜትር፣ በደቡብ ደግሞ እስከ 300 ኪሎ ሜትር ድረስ ዘልቆ ገባ። የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የተቃጣበትን ወረራ ለመመከት ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የእናት ሀገር ጥሪ አስተላለፈ። ሚያዚያ 4 /1969 ዓ.ም በተደረገው የሀገር ጥሪ ከየአቅጣጫው የተሠባሠበ 300 ሺህ የሚሊሻ ሠራዊት በሦስት ወር አሠልጥኖ አስመረቀ፡፡
ሠልጣኙ ከመደበኛው ጦር ጋር በመቀላቀል በከፍተኛ እልህ እና ቁጭት በተሞላበት በጀግንነት እየተፋለመ በአስገራሚ ብቃት የወራሪውን የሶማሌ ጦር ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተጠራርጎ እንዲወጣ ተደረገ። በመጨረሻም የካቲት 26/1970 ዓ.ም ካራማራ ላይ የወራሪው የዚያድባሬ ሠራዊት ዳግም እንዳይለምደው ኾኖ ተመትቶ ሀገሪቱን ለቆ ወጣ፡፡
የካራማራ ድል ከታላቁ የዓድዋ ድል ቀጥሎ ዓለም ያደነቀው ታላቅ ድል ኾኖ በታሪክ ተቀመጠ። ለመኾኑ ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት ለመቋጨቱ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? የሶማሊያ መንግሥት ከ10 ዓመት በላይ ሲያስታጥቁት የኖሩትን የሶቭየት እና የኪዩባ አማካሪዎች ከሶማሊያ በማባረሩ ከባድ የሚባል የመሣሪያ እና መለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት ገጠመው፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ሶሻሊስታዊ የዓለም አቀፍ ወዳጅ መኾኗን ተከትሎ የሶቭየት አማካሪዎች፣ የኪዩባ እና የደቡብ የመን ወታደሮችን በመደገፉ የጦር መሣሪያ ክምችቷ አሻቀበ፡፡
የተዋጊ ሰው ኃይሏም አጅግ እየጨመረ ሄዶ በጥር 1970 ዓ.ም ሰባት ክፍለ ጦሮች ደረሰ፡፡ አንድ ሠራዊት የተሳካ ማጥቃት ለማድረግ ከጠላቱ ቢያንስ ከሦስት እጥፍ በላይ የውጊያ ጥንካሬ ሊኖረው እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። በወቅቱ የሶማሊያ ሕዝብ ብዛት ከኢትዮጵያ 10 እጅ ያነሰ ስለነበር ጦርነቱ እየተራዘመ በሄደ ቁጥር የሶማሊያ ሠራዊት ውጊያውን መቀጠል የሚችልበት ጉልበት እና ሀብት አጣ።
የሶማሊያ የኢኮኖሚ እና የሰው ኀይሏ እና የውጊያ ጥንካሬ ተዳከመ። በአንጻሩ ወረራው ሲጀመር በሰው እና በመሳሪያ ኀይል በእጅጉ ተበልጦ የነበረው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከስድስት ወራት በኋላ ግን በሰው እና በመሣሪያ የበላይነትን መቀዳጀት ቻለ፡፡ የኢትዮጵያውያን ጥልቅ የሀገር ፍቅር፣
የኢትዮጵያ ሠራዊት ጠንካራ መከላከል እና መልሶ ማጥቃት የሶማሊያን ጦር የሰው እና የመሣሪያ ሀብቱን እንዲጨርስ አደረገው። የሶማሊያ ጦር እስከ 700 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ በመግባቱ የአቅርቦት ፈተና አጋጠመው።
የኢትዮጵያ አየር ኀይል የሶማሊያ ታንኮችን፣ ብረት ለበሶችን እና መድፎችን በተጠናከረ መንገድ ማውደም ቻለ። የሶማሊያ ተዋጊ አውሮፕላኖችንም በሰማይ ላይ ውጊያ ማውደሙን ተያያዘው። የኢትዮጵያ አየር ኀይል የሰማይ ላይ ውጊያውን በማሸነፍ እና የሶማሊያን አየር ክልል ጥሶ በመግባት በርካታ ኢላማዎችን አውድሟል፡፡
የመልሶ ማጥቃት ዘመቻው ከተጀመረ በኋላ ወደ ሶማሊያ ድንበር ዘልቆ በመግባት በሀርጌሳ እና በርበራ የሚገኙ አየር ማሪፊያዎችን እና የጦር መሳሪያ ማከማቻዎችን ጭምር ማውደም መቻሉ ለድሉ እንደምክንያት ይጠቀሳሉ።
ይህ ነው ምኞቴ እኔስ በሕይወቴ
ከራሴ በፊት ለኢትዮጵያ እናቴ
ሀገሬ መመኪያ ክብሬ
አትደፈርም ዳር ድንበሬ። በለው ዘምረው ለሀገራቸው በተዋደቁ ጀግኖች ኢትዮጵያ ዳግም ለነካት ሁሉ እሳት መኾኗን አረጋገጠች።
(ኃይለማሪያም ኤፍሬም በ2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል እና የተፈጥሮ መስህብ እና ፋንታሁን አየለ (ዶ.ር) የኢትዮጵያ ሠራዊ ከድል ወደ ውድቀት (ከ1967-1983) በሚል ያሳተሙት መጽሐፍት ምንጮቻችን ናቸው።)
በዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!