ለኢንቨስትመንት የሚደረጉ ውሳኔዎች ጥራትን መሠረት ያደረጉ መኾን እንዳለባቸው ተገለጸ።

16

እንጅባራ: የካቲት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በእንጅባራ ከተማ የተገነቡ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ ፋብሪካዎች እና ሌሎች ፕሮጀክቶች በከፍተኛ የመንግሥት መሪዎች ተጎብኝተዋል። ከእነዚህም መካከል የዱቄት ፋብሪካዎች፣ የሳሙና ማምረቻ፣ የሆቴል ግንባታዎች እና የትራፊክ ኮምፕሌክስ ይገኙበታል።
በተጨማሪም የታሸገ ውኃ ማምረቻ ፋብሪካ እና ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል የመሠረት ድንጋይ ተቀምጧል።

የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው፣ ለኢንቨስትመንት የሚደረጉ ውሳኔዎች ጥራትን መሠረት ያደረጉ መኾን አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል። መሬት ወስደው ያላለሙ ባለሀብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ እና ክትትል መደረግ እንዳለበትም ዋና አሥተዳዳሪው ተናግረዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪ አይተነው ታዴ በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ እና ያለአግባብ ቦታ የያዙ ባለሀብቶች ላይ እርምት እንደሚወሰድ ተናግረዋል። የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ የኔአለም ዋሴ 13 ትላልቅ ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን እና በሦስት ባለሀብቶች ላይ የእርምት እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቡኔ ዓለም እና የአማራ ክልል የመንግሥት ተጠሪ አየን ብርሀን የልማቱ ስኬት የሰላም መረጋገጥ ላይ የተመሠረተ መኾኑን ነው የተናገሩት።

የእናት ዱቄት ፋብሪካ ባለቤት አቶ ዳዊት ባንቲሁን እና የአርዲ ሳሙና ፋብሪካ ባለቤት አቶ ብረሃኑ ፈንታሁን የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ጉብኝት ለተጨማሪ ሥራ እንደሚያነሳሳቸው ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ሰለሞን ስንታየሁ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ80 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የቅርስ ጥገና ሥራ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።
Next articleየካራማራ ተጋድሎ!