
ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት በተከናወኑ ሥራዎች ዙሪያ ከዞን እና ከተማ አሥተዳደሮች የመምሪያ የሥራ ኀላፊዎች እና ከአጋር አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ውስጥ የቅርስ ጥገና ሥራ አንዱ ነው። ቢሮው በመንግሥት በጀት እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ በተለያዩ አካባቢዎች የቅርስ ጥገና እያከናወነ ይገኛል። ትኩረት ከተሰጣቸው አካባቢዎች ሰሜን ወሎ ዞን አንዱ ነው።
የዞኑ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ገነት ሙሉጌታ በ2017 ዓ.ም ለዘመናት ያገለገሉ ቅርሶችን የጥገና ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። በመቄት ወረዳ በ16 ሚሊዮን ብር ወጭ ሦስት የቅርስ እድሳት ሥራ መሠራቱን በማሳያነት አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈ በዞኑ 43 ቅርሶች ጥገና እና እንክብካቤ ሥራ ለመሥራት የቅርስ ልየታ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት። ከተለዩት ውስጥ በላስታ ላሊበላ፣ ጋዞ እና መቄት ወረዳዎች የሚገኙ ቅርሶችን የጥገና ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በዚህ ዓመት መጨረሻ የጥገና ሥራቸው የሚጠናቀቁ ቅርሶች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ፀጋዬ በክልሉ የሚገኙ ቅርሶችን በመጠገን እና መዳረሻዎችን በማልማት ተጨማሪ ምጣኔ ሀብት እንዲያመነጩ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት በመንግሥት እና በማኅበረሰቡ ተሳትፎ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
በዚህ ዓመትም ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ 47 ቅርሶች የጥገና እና እንክብካቤ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ከተመደበው በጀት ውስጥ 40 በመቶ የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ነው ብለዋል። በዩኤስ ኤድ ድጋፍ የደሴ ሙዚየም እድሳት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። የላሊበላ እና አካባቢው ቅርሶች በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ እድሳት እየተደረገላቸው እንደሚገኙም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን