የእግር መጣመም እና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው።

23

ደሴ: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በየዓመቱ ከሚወለዱ ሕጻናት መካከል 200 ያህሉ የአፈጣጠር ችግር ይገጥማቸዋል። ይህንን ችግር ለመፍታት እና ሕጻናትን ለመርዳት የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የአፈጣጠር ችግር ያለባቸውን ሕጻናት የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ዘመቻ ጀምሯል።

በተንታ ወረዳ 01 ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ካሳይቱ ይመር ልጃቸው ሲወለድ የእግር መታጠፍ ችግር እንደነበረበት ተናግረዋል። በዘመቻው በተሰጠ መረጃ አማካኝነት ወደ ደሴ አካል ጉዳተኞች ማገገሚያ ማዕከል በመሄድ ለልጃቸው ሕክምና ማግኘት ችለዋል። ወይዘሮ ካሳይቱ ብዙ ሕጻናት በግንዛቤ እና በመረጃ እጥረት ምክንያት ችግሩን እንደማያስተካክሉ ገልጸው፣ አስፈላጊው የግንዛቤ ሥራ መሠራቱን አብራርተዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ጥላሁን ገስጥ ያልታቀደ እርግዝና ለሕጻናት የአፈጣጠር ችግር መንስኤ እንደኾነ ገልጸዋል። ከችግሩ በኋላም ብዙዎች ችግሩን ከፈጣሪ ቁጣ ጋር በማያያዝ ሕክምና እንደማያገኙ ተናግረዋል። አቶ ጥላሁን ችግሩን ለመከላከል የቅድመ መከላከል ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአፈጣጠር ችግር ያለባቸው ሰዎች ማኅበራዊ መገለል እንደሚደርስባቸው ገልጸው፣ ችግሩ በሕክምና ሊድን እንደሚችል ተናግረዋል። የጤና ችግሩን ለመከላከል የተስተካከለ የምግብ ሥርዓት፣ የቅድመ ወሊድ እና ድህረ ወሊድ ክትትል ማድረግ አስፈላጊ መኾኑንም አስገንዝበዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በአኹኑ ወቅት በደሴ እና ጎንደር ከተሞች ለአምስት ተከታታይ ቀናት የእግር መጣመም እና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ላለባቸው ሕፃናት እና አዋቂዎች የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ነው።

ዘጋቢ፦ ደጀን አምባቸው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleለኢትዮጵያ ልዕልና የሴቶች ሚና ላቅ ያለ መኾኑ ተገለጸ።
Next articleከ80 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የቅርስ ጥገና ሥራ እየተሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ገለጸ።