
ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች እና ባስቀመጣቸው አቅጣጫዎች ላይ የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ አባላት እና ደጋፊዎች ሚና ላይ የሚመክር መድረክ በባሕር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ.ር) ብልጽግና ፓርቲ ሁሉን አቀፍ የኾኑ ውሳኔዎችን ሲወስን የሴቶች ሚና ላቅ ያለ እንደነበር አስታውሰዋል።
ሴቶች ቁጥራችን ብቻ ሳይኾን ስልታችን፣ጥበባችን፣ ሰላም እና ልማት ፈላጊነታችንም ከፍተኛ ነው ያሉት ኀላፊዋ በመተባበር ለምትገነባው ኢትዮጵያ የሴቶች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።ብልጽግና ፓርቲ በየትኛውም ደረጃ ሴቶች ብቁ መሪ እንዲኾኑ እየሠራ መኾኑን ነው ያመላከቱት።
የመንግሥት ሠራተኞች ለሕዝቡ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ይገባቸዋል ያሉት ኀላፊዋ ቆጥረው የተቀበሉትን ሥራ በጥራት ሠርተው ቆጥረው ማስረከብ ይኖርባቸዋል፣ በዚህ ረገድ አሁን ላይ ያለውን በጎ ጅማሮ ለማስፋፋት ብልጽግና እየተጋ ነው ብለዋል።
ለኢትዮጵያ ልዕልና የሴቶች ሚና ከፍተኛ በመኾኑ ለሁለንተናዊ ብልጽግና በትብብር መሥራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። የብልጽግና ዋና ዓላማም ኢትዮጵያን በሁሉም መስክ ማሳደግ መኾኑን ተናግረዋል።
ጠንካራ ፓርቲ ባለበት ሀገር ጠንካራ መንግሥት ይኖራል ብለዋል። ጠንካራ መንግሥት ደግሞ ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር ይወስናል ነው ያሉት። ሁላችንም ለብልጽግና የበኩላችንን አስተዋጽኦ በማበርከት ኢትዮጵያን ማሳደግ ይገባናል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ክንፍ ሥራ አስፈጻሚ እና የሲዳማ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፈንታዬ ከበደ የአማራ ክልል ሴቶች ከሌሎች ክልሎች አቻዎቻቸው ጋር በመኾን ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ወቅት ስንቅ በማዘጋጀት፣ ትጥቅ በማቀበል እና ቁስለኞችን በመንከባከብ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያን በመገንባቱ ሂደት አይነተኛ ሚና መጫወታቸውንም ተናግረዋል።
ሴቶች ዘርፈ ብዙ ጥበብ እና ዕውቀት ስላላቸው ለሰላም ዘብ ከመቆም ባሻገር የኢትዮጵያን ብልጽግና አብሳሪ ናቸው ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ የምክር ቤት አባል ሕይዎት ኃይሉ በድብቅ ብጥብጥ እየጠነሰሱ የሚጠምቁትን ማጋለጥ ይገባናል ነው ያሉት።
በርካታ ሕጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መኾናቸውንም አንስተዋል። እነዚህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሌላዋ ተሳታፊ ትዕግስት ጌታቸው የሰላም አደናቃፊዎችን በመድረክ ከመታገል ባለፈ አካባቢያቸውን በንቃት እየጠበቁ መኾናቸውን ተናግረዋል። ሁሉም የኀብረተሰብ ክፍል ሰላሙን ካስከበረ የሀገራችን ብልጽግና ሩቅ አይደለም ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን