
ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በ2017 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የተከናወኑ ሥራዎች ዙሪያ ከዞን እና ከተማ አሥተዳድሮች የመምሪያ የሥራ ኀላፊዎች እና ከአጋር አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
የአማራ ክልል የበርካታ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶች መገኛ ነው። የክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየዉ በክልሉ 27 አይነት፣ በመጠን ደረጃ ደግሞ 2 ሺህ 298 ለቱሪዝም መዳረሻነት መዋል የሚችሉ ሀብቶች ይገኛሉ። ሰፊ የቱሪዝም መዳረሻ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች ውስጥ ደግሞ ሰሜን ወሎ ዞን አንዱ ነው።
በዞኑ በ2017 በጀት ዓመት የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ሥራ በመሠራቱ ከ3 ሺህ 800 በላይ የውጭ ሀገር ዜጎች መጎብኘታቸውን የዞኑ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ገነት ሙሉጌታ ገልጸዋል። ከ24 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢም ተገኝቷል ነው ያሉት። ላሊበላ እና አካባቢውን ከጎበኙት ደግሞ ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ብር እንድኹም ከሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ደግሞ 638 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ነው ኀላፊዋ የገለጹት።
ከባለፉት ሁለት ዓመታት የተሻለ የጎብኝዎች ቁጥር አካባቢውን በመጎብኘታቸው ተዘግተው የነበሩ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል። ለ1 ሺህ 200 ዜጎችም በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሥራ እድል ተፈጥሯል ነው ያሉት። የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ በ2017 በጀት ዓመት ከመስከረም ወር ጀምሮ የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት አሳይቷል ብለዋል።
እስከ ጥር አጋማሽ ከ16 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር እና ከ5 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ክልሉን ጎብኝተዋል ነው ያሉት። ከዚህም ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ገቢም ተገኝቷል ብለዋል። ይህም የዕቅዱን 63 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው የገለጹት። በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር ለዕቅዱ አለመሳካት ምክንያት እንደኾነም ኀላፊው ገልጸዋል።
የግማሽ ዓመቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ካለፉት ሁለት ዓመታት የተሻለ እንደኾነም አንስተዋል። በበጀት ዓመቱ በሆቴል፣ በቅርስ ጥገና፣ በዕደ ጥበብ ውጤቶች እና በመሳሰሉት ዘርፎች ከ26 ሺህ በላይ ለሚኾኑ ዜጎች በቋሚነት እና በጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ነው ያሉት።
በበጀት ዓመቱ በተፈጠረው ሰላም ከሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት ጀምሮ እስከ ጥምቀት ድረስ ያሉ በዓላትን በድምቀት በማክበር የክልሉን ገጽታ መቀየር ተችሏል ብለዋል።
የክልሉን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በተለያዩ ሚዲያዎች በማስተዋወቅ እና በጉዞ ማኅበራት በኩል በማስጎብኘት የገጽታ ግንባታ ተግባር እየተሠራ ይገኛል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!