በጎንደር ከተማ 2 ሺህ 600 ነጋዴዎች በአዲስ ወደ ንግድ መረቡ እንዲገቡ ተደርጓል።

19

ጎንደር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ሕገ ወጥ ንግድን በመከላከል እና ገበያ በማረጋጋት ሥራዎች ላይ ያተኮረ ውይይት ከአጋር አካላት ጋር አካሂዷል።

መምሪያው ሕገ ወጥ ንግድን በመከላከል ጤናማ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር እየሠራ መኾኑ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

በጎንደር ከተማ 16 ሺህ የሚደርሱ ነጋዴዎች እንዳሉ የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ንግድ እና ገበያ ልማት መምሪያ ኀላፊ ቴዎድሮስ ፀጋየ ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ 2 ሺህ 600 ነጋዴዎች በአዲስ ወደ ንግድ መረቡ እንዲገቡ መደረጉንም ገልጸዋል።

የሕገ ወጥ ንግድን እና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪን ለመግታት የግብይት ማዕከላትን ማስፋት እና መሠረታዊ የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ማጠናከር አስፈላጊ በመኾኑ ለዚህም እየተሠራ መኾኑን ኀላፊው ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ደብሬ የኋላ ሰው ሠራሽ ምክንያቶች የንግዱን እንቅስቃሴ ጤናማ እንዳይኾን ያደርጋሉ ብለዋል። የሕገ ወጥ ነጋዴዎች መስፋፋት ጤናማ የሆነውን የንግድ እንቅስቃሴ የሚያውክ በመኾኑ ሁሉም ባለደርሻ አካላት ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በከተማ አሥተዳደሩ ወደ ኅብረተሰቡ ቢደርሱ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ግምታዊ ዋጋቸው 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሆነ የተለያዩ ምግቦች መወገዳቸውም በመድረኩ ላይ ተነስቷል።

ዘጋቢ:- ዳንኤል ወርቄ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር ከስዊድን ፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በፍልሰት እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አካሄደ።
Next article“የሰላም እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ መመለስ ይገባል” አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ