
ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ውይይቱ በኢትዮጵያ ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ እና በስዊድን ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አንዴርስ ቶር ሃል መካከል ነው የተካሄደው።
በላይሁን ይርጋ ኢትዮጵያ እና ስዊድን በተለያዩ ዘርፎች አብሮ በመሥራት በኩል የቆዬ ግንኙነት እንዳላቸዉ አስታውሰው ስዊድን ለኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ለምታደርገዉ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ የፍልሰት እና የስደት አሥተዳደርን በሚመለከት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየወሰደች ስላለችው የሕግ፣ የፖሊሲ እና ተግባራዊ እርምጃዎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያም ሰጥተዋል።
ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ጨምሮ መደበኛ ያልኾነ ፍልሰት አኹንም ፈተና እንደኾነ አንስተዋል። ጉዳዩ የሀገራትን ቅንጅት እና ትብብር የሚፈልግ እንደኾነም አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ የምታስተናግድ ሀገር መኾኗን ያነሱት ሚኒስትር ዴኤታው የስዊድን መንግሥትም በእነዚህ እና በሌሎች ከፍልሰት ጋር ተያያዥ በኾኑ ጉዳዮች ላይ ድጋፉን እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
የስዊድን ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አንዴርስ ቶር ሃል ሀገራቸዉ ስዊድን እና ኢትዮጵያ በፍትሕ፣ ኢኮኖሚ እና በሌሎች ዘርፎች አብረው ሢሠሩ መቆየታቸዉን አንስተዋል። ወደፊትም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በተለይም በፍትሕ ዘርፉ ልምድን በመለዋወጥ፣ በአቅም ግንባታ ሥራዎች እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ መንግሥታቸዉ አብሮ እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የሚተገበሩ ሥራዎችን በተመለከተም በየጊዜዉ የክትትል ሥራ እንደሚሠራም የፍትሕ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!