የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ።

26

ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር እና የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የቱሪዝም ዘርፉን ማነቃቃት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መስፍን ጣሰው ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለስቶፕ ኦቨር ቱሪዝም ያላትን ሰፊ ዕድል መነሻ በማድረግ ዘርፉ እንዲስፋፋ፣ እንዲጎለብት እና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ የሚያስችል የትብብር ማዕቀፍ ለመዘርጋት ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ መስፍን ጣሰው የተፈረመው ስምምነት መንገደኞች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት አንስተዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው አየር መንገዱ በዘርፉ ትልቅ አቅም እንዳለው በመግለጽ ስምምነቱ ታሪካዊ እና የተፈጥሮ የቱሪስት መዳረሻዎች በስፋት እንዲጎበኙ ያደርጋል ብለዋል።

ስምምነቱ ተቋማቱ ሥራቸውን በተቀላጠፈ መልኩ እንዲያከናውኑ ያግዛል ያሉት ደግሞ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት ናቸው።

ኤፍቢሲ እንደዘገበው ስምምነቱ የአዲስ አበባን የቱሪዝም ዕድገት ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ እና በከተማዋ የቆይታ ግዜ ለሚኖራቸው መንገደኞች በተዘጋጀ ስቶፕ ኦቨር ፓኬጅ ላይ በጋራ ለመሥራት እንደሚያስችል ተመላክቷል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከፍተኛ መሪዎች በእንጅባራ ከተማ ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ።
Next articleሚዛኑን የጠበቀ ልማት እና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በፖለቲካው የሴቶች ተሳትፎ ጎልቶ መታየት አለበት።