ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።

19

ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ቢሮው ከአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ጋር በመተባበር ያስለማውን ዌብሳይት ተረክቧል። ቴክኖሎጁው ፍትሕ ቢሮ ያዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ እስከ ወረዳ ለማድረስ እንደሚያግዝም ነው የተገለጸው።

የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኀላፊ ብርሃኑ ጎሽም ቢሯቸው የሚሰጠው አገልግሎት ሰፊ መኾኑን ጠቅሰው የተቀላጠፈ፣ ውጤታማ እና ተደራሽ የኾነ አገልግሎት ለመስጠት በቴክኖሎጂ የመታገዙን አስፈላጊነት አንስተዋል።

በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮን ላበለጸገው ሶፍትዌር አመስግነዋል። ዌብሳይቱ ፍትሕ ቢሮን ለማስተዋወቅ እና ለአጠቃቀም ምቹ መኾኑንም አንስተዋል።

የአማራ ክልል ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኀላፊ አቤል ፈለቀ በበኩላቸው የበለጸገውን ሶፍትዌር ማስረከብ ብቻ ሳይኾን በየጊዜው ድጋፍ በማድረግ የማሻሻል እና የማጎልበት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል።

ኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ቢሮ ያበለጸገውን ሶፍትዌር ለፍትሕ ቢሮ ማስረከቡን ተከትሎ የእውቅና እና ምስጋና ሥነ ሥርዓትም ተከናውኗል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ከተማውን የሚያነቃቁ ናቸው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleከፍተኛ መሪዎች በእንጅባራ ከተማ ተገንብተው ወደ ሥራ የገቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ።