“በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ የልማት ሥራዎች ከተማውን የሚያነቃቁ ናቸው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

24

ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባሕር ዳር ከተማ እየተሠራ ያለው የኮሪደር ልማት ተግባር በጥሩ ኹኔታ እየሄደ ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማቱ ለነዋሪዎች ምቹ ኹኔታን የሚፈጥር መኾኑንም ገልጸዋል። ጣናን ከልለውት የነበሩ አካባቢዎች ለምተው መከፈታቸውንም ተናግረዋል። በኮሪደር ልማቱ የሚቀሩ የመብራት ሥራዎችም በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቁ አይተናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመብራት ፖል በክልሉ እየተመረተ መኾኑንም ገልጸዋል።

የባሕር ዳር የኮሪደር ልማት በክልሉ በተመረቱ ጥሬ እቃዎች የሚሠራ መኾኑንም አንስተዋል። የተጀመረውን የኮሪደር ሥራ አጠናቅቆ ወደ ሌላ የኮሪደር ልማት መግባት ይገባል ነው ያሉት። የልማት ሥራዎችን ጥራት እና ዘላቂነት መጠበቅ ይገባልም ብለዋል። የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲዮም የካፍ እና የፊፋ ደረጃዎችን ባሟላ መልኩ እየተገነባ መኾኑንም ነው ያነሱት። ሳር ተተክሏል፣ አሳንሰር ተገጥሟል፣ ወንበርም እየተገጠመለት ነው ብለዋል።

የመልበሻ ክፍሎች እና ሌሎችም እየተሠሩለት መኾኑን መመልከታቸውንም ተናግረዋል። ስታዲዮሙ በዓመቱ መጨረሻ አካባቢ ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚችልበት አማራጭ እንዲኖር ኾኖ እየተሠራ ነው ብለዋል። የስታዲዮሙ ግቢ ውብ ኾኖ መሠራቱንም ገልጸዋል። የአማራ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና ማሽን ቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝን መጎብኘታቸውን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢንዱስትሪው ታላላቅ ሥራዎችን እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ኢንዱስትሪው ያቀረባቸው ጥያቄዎች እንዲፈቱ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ያለው አቅም እና ማሽነሪ ትልቅ መኾኑን ተናግረዋል። በከተማዋ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን መመልከታቸውንም ገልጸዋል። የተደራጁ ወጣቶች በሌማት ትሩፋት ተጠቃሚ እየኾኑ ነው ብለዋል። የተጀመሩ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገም ገልጸዋል። “በከተማዋ እየተሠሩ ያሉ ሁሉም የልማት ሥራዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ ከተማውን የሚያነቃቁ ናቸው” ብለዋል።

ባሕር ዳር ሰላም መኾኗን በእግራችን ተንቀሳቅሰን አይተናል፣ ሕዝቡም እየተዝናና ተመልክተናል ነው ያሉት። ባለሀብቶች ሥራቸውን እየሠሩ መኾናቸውንም አስተውለናል ብለዋል። ያለውን ሰላም ማጽናት እና ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት። ከክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸውንም ገልጸዋል። በቆይታቸው ደስተኛ መኾናቸውንም ተናግረዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የበልግ አብቃይ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ።
Next articleቴክኖሎጂን በመጠቀም ተደራሽነቱን ለማስፋት እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ አስታወቀ።