
ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ባወጣው መግለጫ መሠረት በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት በመካከለኛው፣ በሰሜን ምሥራቅ፣ በምሥራቅ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ ቦታዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ። እነዚህ አካባቢዎች የበልግ ዋና የዝናብ ጊዜያቸውን እያሳለፉ ነው።
በእነዚህ አካባቢዎች የሚጠበቀው መካከለኛ መጠን ያለው እርጥበት ለበልግ የእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ይሁን እንጂ ከበልግ ተለዋዋጭ ባህሪ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ደረቃማ ጊዜያት እና ከፍተኛ ትነት የአፈር ውስጥ እርጥበት እጥረት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን ጥንቃቄ የተሞላበት ተግባራትን አስቀድመው ማከናወን ይኖርባቸዋል።
በበልግ አብቃይ አካባቢዎች የሚጠበቀው መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ የአፈር ውስጥ እርጥበትን በማሻሻል በዚህ ወር ለሚዘሩ ሰብሎች የማሳ ዝግጅት፣ የሰብል ዘር መዝራት፣ ለቋሚ ተክሎች የውኃ አቅርቦት እና አቅርቦትን ከማሻሻል አንጻር አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል።
በመኾኑም አርሶ አደሮች የበልግ ወቅትን እንዲሁም የግጦሽ ሳር እና የመጠጥ ውኃን በተመለከተ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ አስፈላጊ የዘር ግብዓቶችን አስቀድመው ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ በወሩ በአንጻራዊነት ደረቃማ ቀናት ስለሚኖሩ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኘውን የዝናብ ውኃ በማሠባሠብ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ያስፈልጋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!