
ባሕር ዳር: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዘመኑ በዋጀው የማኅበራዊ ቴክኖሎጅ አጠቃቀም እና የመረጃ ተደራሽነት ፍጥነት ምክንያት ዓለም አንድ መንደር እንድትመስል አድርጓታል። ይህ ብቻም ሳይኾን የመተግበሪያ መንገዶቹም በየጊዜው ሲቀያየሩ እና ሲለዋወጡ የሚታይበት ዘመነ ቴክኖሎጅ ላይ እንገኛለን።
ዊ አር ሶሻል ሚዲያ የተሰኘው የሞኒተሪንግ ኩባንያ እንዳስነበበው በአሁኑ ሰዓት የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከአምስት ቢሊዮን በላይ እንደደረሰ ገልጿል። ይህ ቁጥር ደግሞ በዓለም ላይ ካሉ ሕዝቦች ውስጥ 62 ነጥብ 3 በመቶ የሚኾነውን እንደሚሸፍንም ጠቅሷል። ሪፓርቱ እንዳሳየው የማኅበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከዓመት ዓመት በፍጥነት እየጨመረ ሄዷል።
እየዘመነ የመጣውን የቴክኖሎጅ ውጤት ጥንቃቄ በተሞላበት እና ለበጎ ዓላማ ካለመጠቀም የሚመጡ መዘዞችም የሚስተዋሉበት ኾኗል። ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ታድያ ሀገራት እንደየ እድገታቸው እና እንደየሚፈልጉበት አንግል ለማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሕግ ደንግገውለታል።
አብርሃም አሳዬ በምዕራብ ጎንደር ዞን ፍትሕ መምሪያ ውስጥ የወንጀል አቃቢ ሕግ ባለሙያ ናቸው። ማኅበራዊ ሚዲያ አሁን ላይ የዓለም ሕዝቦች በስፋት እየተጠቀሙበት ያለ የዘመኑ ውጤት ነው ይላሉ።
ማኅበራዊ ሚዲያ የሕግ ትርጉም የተሰጠው ነው ብለዋል የአቃቢ ሕግ ባለሙያው አብርሃም አሳዬ። በሀገራችን ሕግ ላይም የጥላቻ ንግግር እና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል በሚል 1185/2012 የወጣው የሕግ መመሪያ ላይ ማኅበራዊ ሚዲያ ምንድን ነው በሚል ተቀምጧል ብለዋል። አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 8 ላይም ተርጉም አስቀምጦታል።
ይህም ማኅበራዊ ሚዲያ ማለት ሰዎች መልዕክትን ለመለዋወጥ፣ ትስስርን ለማዳበር፣ ሃሳብን ለመጋራት በኢንተርኔት አማካኝነት በአንድ ጊዜ ለበርካታ ሰዎች መረጃ የሚደርስበት መንገድ ስለመኾኑ ሕጉ አስቀምጦታል ብለዋል። የአቃቢ ሕግ ባለሙያው ማኅበራዊ ሚዲያ የራሱ የኾኑ አሉታዊ እና አወንታዊ ጎኖች ያሉት በመኾኑ አጠቃቀሙን አስመልክቶ ሕግ የተበጀለት እንዲኾን ተደርጓል ነው ያሉት።
አወንታዊ ጎን ብለው ከሚጠቅሱት ውስጥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ክህሎትን ያዳብራል፤ የንባብ መድረክ ኾኖ በማገልገል ግንዛቤ እንዲያድግ ያደርጋል፤ የዕውቀት ምንጭ ኾኖ ያገለግላል፤ የፈጠራ ሥራዎች ምንጭ ይኾናል፤ በጥቅል ደግሞ ሰዎች ዓለምን እንዲረዱ እና እንዲያውቁ በማድረግ በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው ብለዋል።
እንደ አቃቢ ሕግ ባለሙያው ገለጻ ማኅበራዊ ሚዲያን በሠለጠነ እና ለበጎ ጉዳይ ካልተጠቀምንበት አሉታዊ ጎኑም ከፍተኛ እንደኾነ ገልጸዋል። በተለይ ደግሞ ባላደጉ ሀገራት ላይ በአጠቃቀም ጉድለት ሳቢያ ተጽዕኖው ቀላል አይደለም ነው ያሉት። ከአጠቃቀም ጋር በተያያዘ ሁሉም የሚለቀቁ ነገሮች እውነት ናቸው ብሎ መቀበል ስህተት እንደኾነም ይጠቁማሉ።
ነገሮችን በጥልቀት እንዳናስብ፣ እንዳንመረምር እና እንዳናገናዝብ በማድረግ ለተለያዩ ችግሮች የማጋለጥ ዕድሉ ሰፊ ነው ይላሉ። ማኅበራዊ ሚዲያን በአግባቡ ካለመጠቀም ባሕል፣ ወግ፣ ልማድ እና እሴት ፈተና ሊገጥማቸው ይችላል ባይ ናቸው። በአግባቡ ካለመጠቀም ጊዜ በከንቱ ሊባክን ይችላል፤ ሰውን ከሰው በማጋጨት ለሰላም እጦት እንደ ምንጭ ይኾናልም ነው ያሉት። መረጃን ከዕውነታው በማራቅ እና እንዳይረጋጉ በማድረግም ወደትልቅ ሀገራዊ ቀውስ ሊከት ይችላል፤ ይህም በተግባር ተስተውሏል ብለዋል።
ዓለም ዓቀፍ የፓለቲካ እና የግለሰብ መብቶች ኮንቬንሽን አንቀጽ 19 ላይ ሃሳብን በነጻነት ስለመግለጽ ይደነግጋል። እዚሁ ኮንቬንሽን አንቀጽ 20 ላይ ግን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሊገደብ እንደሚችልም አስቀምጧል ነው ያሉት የአቃቢ ሕግ ባለሙያው አብርሃም አሳዬ። ክልከላዎች ደግሞ በሕግ የተተረጎሙ ናቸው ብለዋል።
በሀገራችን ሕገ መንግሥት አንቀጽ 9 ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መርህ ተደርጎ የተደነገገ ቢኾንም አንቀጽ 29 ላይ ደግሞ መብቱ በሕግ ሊገደብ እንደሚገባው አስቀምጧል ይላሉ። ይህም የሚኾነው የሕዝቦችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል እንደኾነ አስረድተዋል። ይህን ለመከላከል 1185/2012 ዓ.ም ላይ የወጣው የጥላቻ ንግግር እና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ በግልጽ አስቀምጦታል ብለዋል።
በተቀመጠው ሕግ መሠረትም ተጠያቂነትም እንዳለው አስገንዝበዋል። ተጠያቂነቱም እንደተሠራው ጥፋት ታይቶ የገንዘብ ወይም የእስራት ሊኾን ይችላል ነው ያሉት። ምሳሌ ከ5 ሺህ በላይ ተከታይ ያለው አካል ማንኛውንም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቅሞ የጥላቻ ንግግር ወይም ሀሰተኛ መረጃ ያሰራጨ እንደኾነ እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት እና እስከ 100 ሺህ ብር እንደሚቀጣ አንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ተቀምጧል ብለዋል። ሌሎች የቅጣት እርምጃዎችም እንዳሉ አስረድተዋል።
እንደ ሀገር በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ውስንነት ሳቢያ እየደረሱ ያሉ ችግሮች በእጅጉ ሰፊ እንደኾኑ የአቃቢ ሕግ ባለሙያው በአጽንኦት ያወሳሉ። በአግባቡ ባለመጠቀማችንም ለውስብስብ ችግር እየተዳረግን እንገኛለን ነው ያሉት። ከሕግ አንጻር የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሙ ላይ ግልጽ ያልኾኑ እና አሻሚ ነገሮችን ማጥራት ቢቻል የሚል ምክረ ሀሳባቸውንም ገልጸዋል። ይህም በዋናነት መንግሥትን የሚመለከት ነው ብለዋል። ለአብነት ብለው ዝርዝር ነገሮችን በግልጽ ማስቀመጥ ላይም የበለጠ መሥራት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ለምሳሌ ይህን ጉዳይ የሚመለከተው አዋጅ 1185/2012 ላይ የተለቀቀውን መልእክት መውደድ ወይም ላይክ ማድረግ እና መለጠፍ ወይም ታግ ማድረግ አያስቀጣም ይልና ማጋራት ወይም ሸር እና ሰብስክራይብ የሚለውን ደግሞ ሕጉ ሲመልስ አይታይም ባይ ናቸው። በዚህም ምክንያት ሕጎች በዝርዝር እና በግልጽ መታየት አለባቸው ባይ ናቸው።
አሉታዊ መንገዶችን በውል በመረዳት ማኅበራዊ ሚዲያን ከበጎ ተግባር በተቃረነ መልኩ መጠቀምን ማስቀረት ግን ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ግዴታ እንደኾነም ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ሰለሞን አንዳርጌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!