የገጠር መንገድ ትስስርን ተደራሽ ለማድረግ ወደ ሥራ ተገብቷል።

26

አዲስ አበባ: የካቲት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የገጠር መንገድ ትስስርን ተደራሽ በማድረግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የገጠር መንገድን ከዋና መንገዶች ጋር ለማስተሳሰር የሚያስችል ከመንግሥት እና ከዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ የ407 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱን የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት አንስተዋል።

የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ፍትሐዊ እና አካታች የኾነ የመንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሸ ማድረግ ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

በተለይም እንደ ሀገር የገጠር መንገዶችን ከዋና መንገዶች ጋር የሚያገናኙ በቂ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ማፋጠን የፕሮጀክቱ ተቀዳሚ ዓላማ መኾኑን አንስተዋል።

እንደ ሀገር በቂ የመንገድ መሠረተ ልማት ባለመሟላቱ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ዜጎች ላልተፈለገ እንግልት እና ስቃይ እየተዳረጉ መኾኑን ነው የገለጹት።

ባለድርሻ አካላት የወገኖቻችን ሥቃይ በመገንዘብ እና የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አሳስበዋል። ለተግባራዊ ተፈጻሚነቱም መሪዎች መናበብ፣ መቀናጀት እና መግባባት አለባቸው ብለዋል።

እንደ ሀገር አኹን ላይ ያለው የመንገድ አውታሮች መጠን 171 ሺህ ኪሎ ሜትር ሲኾን በአስር ዓመት ውስጥ የሀገሪቱን የመንገድ አውታር 245 ሺህ ኪሎ ሜትር ለማድረስ እየተሠራ መኾኑንም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱን በአግባቡ መተግብር ከተቻለ የድጅታል ገበያ ትስስርን፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማምጣት እና ከፍተኛ የሥራ ዕድልን ለመፍጠር የሚያስችል ነው ተብሏል።

በመድረኩ የመሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የመንገድ እና ትራንስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እንዲኹም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዘጋቢ: ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በባሕር ዳር የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ጎበኙ።
Next article“ዕቅዳችን እና መዳረሻችን ኢትዮጵያን ያማከለ ሰው ተኮር ተግባር መኾን አለበት” መሉነሽ ደሴ (ዶ.ሴ)