
ባሕር ዳር: የካቲት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከውስጥ እና ከውጭ ተሳስረው የከፈቱብንን ጥቃት እንደ ትናንት የዓድዋ ጀግኖች አባቶቻችን ሁሉ በመስዋዕትነታችን ድል እንነሳቸዋለን” ሲሉ የአማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኀላፊ በሪሁን መንግሥቱ
አስታውቀዋል።
ምክትል ቢሮ ኀላፊው ደቡብ ጎንደር ዞን እብናት ወረዳ ተገኝተው የጸጥታ መዋቅር አባላትን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ አወያይተዋል።
ይህን የእርስ በርስ የመጠፋፋት እና አሸናፊ የሌለው ግጭት ለሕዝባችን የማይበጅ እና ሀገርን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ በመኾኑ በቁርጠኝነት ታግለን ልናስተካክለው ይገባል ነው ያሉት።
አቶ በሪሁን በየትኛውም ዘመን እና የታሪክ አጋጣሚ እርስ በእርስ በመገዳደል፣ በመጠፋፋት እና የሕዝብን ሀብት እና ንብረት በማውደም የዕድገት ማማ ላይ የደረሰ ሕዝብም ኾነ”ችግሩን በኃይል የፈታ ሀገር የለም” ብለዋል።
ዘራፊው ቡድን ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር ትስስር ፈጥሮ ታሪካዊ ስህተት በመፈጸም የአማራን ሕዝብ ወደ ተወሳሰበ ችግር ውስጥ እየከተተው በመኾኑ ልንነቃበት ይገባል ብለዋል።
መንግሥት የሰላምን መንገድ መርጦ ሰፊ ጥረት ቢያደርግም የሰላምን አማራጭ ረግጦ በመጠፋፋት ሀገር አቀናለሁ በሚል እብሪት በርካታ ግፎችን እየፈጸመ ይገኛል ነው ያሉት።
“በሕዝባችን ሙሉ ድጋፍ፣ በጸጥታ መዋቅራችን እልህ አስጨራሽ ትግል እና በመሪዎች ሰፊ ጥረት የጠላትን ክልሉን የማፍረስ ህልሙን አምክነነዋል” ብለዋል።
አሁንም ከፊት ለፊታችን ያለውን ትግል ለመቋጨት እና በሕዝባችን ላይ የተጫነውን ባርነት እና ግፍ ለማስቆም የጸጥታ መዋቅራችን ከመቸውም ጊዜ በላይ በጽናት መቆም እና ኀላፊነትን መወጣት ይገባል ነው ያሉት።
ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ሕዝባችን እና ሀገራችን ከጥፋት ለመታደግ አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ ለመክፈል ተዘጋጅተናል ብለዋል።
በቅርብ ጊዜ ለሕዝባችን የተሟላ ሰላምን እናበሥራለን ማለታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያሳያል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!