
ባሕር ዳር: የካቲት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ያገኛቸውን የግብርና ምርምር ሥራዎች የሚገመግምበት አውደ ጥናት እያካሄደ ነው።
በአውደ ጥናቱ የተገኙት በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ባገኛቸው የምርምር ሥራዎች የክልሉ የግብርና አማካይ ምርታማነት ከነበረበት 10 ኩንታል በሄክታር አሁን ላይ ወደ 32 ኩንታል በሄክታር ማሳደግ እንደተቻለ ተናግረዋል። በዚህም በክልሉ የግብርና ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
አሁን ላይ የዓለም አማካይ የግብርና ምርታማነት 40 ኩንታል በሄክታር መኾኑን የጠቀሱት ዶክተር ድረስ ሳህሉ ከዚህ አሐዝ ለመድረስ፣ የክልሉን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እና የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚውን ለማሸጋገር ምርምር ኢንስቲትዩቱ ከዚህም በላይ በትኩረት መሥራት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የመንግሥት የልማት አጀንዳዎች የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ግብርናውን ወደ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር እና ከውጭ የሚገባውን የግብርና ምርት በሀገር ውስጥ መተካት መኾኑን ነው ዶክተር ድረስ የተናገሩት። የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ይህን ግብ በማሳካት በኩል ትልቅ ኀላፊነት ያለበት ተቋም በመኾኑ የሚሠሩ የምርምር ሥራዎች ከመንግሥት የልማት እቅዶች ጋር የተጣጣሙ መኾን አለባቸው ብለዋል።
የምርምር ተቋሙ የሚያፈልቃቸውን የግብርና እውቀቶች እና ቴክኖሎጅዎችን የክልሉ ግብርና ቢሮ ሰፊ የኤክስቴንሽን ሥራ በመሥራት ለሁሉም ተደራሽ እንዲኾኑ በትኩረት ይሠራልም ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ በሁለንተናዊ ዘርፎች መጠናከር አለበት ያሉት ቢሮ ኀላፊው ተቋሙን ለማጠናከር የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ፍላጎት አለው፣ ለዚህም በትኩረት እየሠራበት ነው ብለዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አስማረ ደጀን (ዶ.ር) በበኩላቸው የምርምር ኢንስቲትዩቱ የሕዝቡን እና የመንግሥትን የልማት ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የምርምር ሥራዎችን በትኩረት እየሠራ ስለመኾኑን ገልጸዋል።
በምርምር ሥራዎች ግምገማ ቀርበው የሚታዩ የምርምር ሥራዎችም ይህን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ውጤታማ እንዲኾኑ ለማስቻል ነው ብለዋል።
የምርምር ኢንስቲትዩቱ 282 አዲስ፣ 426 በሂደት ላይ ያሉ እና 213 የተጠናቀቁ በአጠቃላይ 921 የምርምር ሥራዎች አቅርቦ እያስገመገመ ነው።
በአውደ ጥናቱ ከዓለም አቀፍ የምርምር ተቋማት የተጋበዙ ተመራማሪዎች፣ የኢንስቲትዩቱ እና የምርምር ማዕከላት ተመራማሪዎች፣ በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እየተሳተፉ ናቸው፡፡ መረጃው ከኢንስቲትዩቱ ድረ ገጽ የተገኘ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን