የሃይማኖት አገልጋዮች በሕዝቦች አንድነት፣ ሰላም፣ ፍትሕና እኩልነት ላይ አጥብቀዉ ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ አሳሰቡ።

76

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት 12ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተከብሯል።

ብጹዕ አቡነ ማትያስ በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልእክት እግዚአብሔር ካህናትን በጎቹን በንጽህና እና በቅድስና እንድንጠብቅ፤ በምድር ላይ ሰላምና ሰላም ብቻ እንድናውጅ፤ ፍትሕ እንዳይዛባ እንድንመክር፣ አንድነትና እኩልነት እንዳንነጣጥል፣ ፍቅርና ይቅርታ እንዳይቀዘቅዝ ሌት ተቀን እንድናስተምር የሰላም ወንጌልን አስጨብጦናልና፤

በቤቱ ሆነን የምንሰጠው አገልግሎት ለባለቤቱ የሚመጥን መኾኑን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።

የሃይማኖት አገልጋዮች በሕዝቦች አንድነት፣ ሰላምና እኩልነት ላይ አጥብቀዉ ማስተማር እንደሚኖርባቸዉም አሳስበዋል።

ለአሁኑ ዘመን የማይመጥኑ ብዙ የሥራ አፈጻጸሞች አሉብን ያሉ ሲሆን እነዚህን በማስተካከል ወደ ተሻለ የሥራ አፈጻጸም ለመሸጋገር ካህናት እንዲሁም ሕዝበ ክርስቲያኑ የበኩሉን ኀላፊነት መወጣት እንደሚኖርበት መክረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ 12ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሃይማኖት መሪዎች፤ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ኃላፊዎች፤ የገዳማትና አድባራት አሥተዳዳሪዎች፤ ካህናትና ምዕመናን በተገኙበት መከበሩን ኢፕድ ዘግቧል።

Previous articleጥራት ያለው እና ፍትሐዊ የኾነ የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next articleየዓለም አቀፍ እና ቀጣናዊ አጋር ድርጅቶች አመራሮች ሕዳሴ ግድብን ጎበኙ።