
አዲስ አበባ: የካቲት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የአፈጣጠር ችግር ሳምንት “የላቀ ብሔራዊ የመከላከል ሕክምና እና አካታች ሥርዓት ለአፈጣጠር ችግሮች” በሚል መሪ መልዕክት በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በመድረኩ በጤና ሚኒስቴር የጤና አገልግሎት መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ኢሊባቡር ቡኖን (ዶ.ር)፣ የዓለም ጤና ድርጅት የሥራ ኀላፊዎች፣ የለጋሽ እና አጋር ድርጅት መሪዎች፣ የሙያ ማኅበራት ኀላፊዎች እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
የጤና አገልግሎት መሪ ሥራ አሥፈጻሚ ኢሊባቡር ቡኖን (ዶ.ር) መንግሥት በጤናው ዘርፍ ትኩረት አድርጎ ከሚሠራቸው የልማት እና የኢንቨስትመንት ዕቅዶች ውስጥ ጥራት ያለው እና ፍትሐዊ የኾነ የጤና አገልግሎት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ተደራሽ ማድረግ ነው ብለዋል።
ይህንን ግብ ለማሳካትም የማኅበረሰቡን እና የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ማሳደግ፣ መሠረተ ልማትን ማጠናከር፣ የሰው ኃይልን ማሠልጠን፣ ጥናትና ምርምር ማድረግ እና ግብዓቶችን ማሟላት ተቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል።
እነዚህን ችግሮች ለመከላከልም በሁሉም የጤና ተቋማት እናቶች በድህረ ወሊድ እና በቅድመ ወሊድ የጤና ክትትል እንዲያደርጉ፣ ክትባት እንዲወስዱ፣ የተሻለ የአመጋገብ ሥርዓት እንዲኖራቸው በማሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እየተሠጡ መኾኑን አንስተዋል።
ጥራት ያለውና ፍትሐዊ የኾነ የህክምና አገልግሎት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ተደራሽ በማድረግ የአካል ጉዳተኝነትን እና የአፈጣጠር ችግርን መከላከል እንደሚገባም ነው የገለጹት።
አገልግሎቱ ሁሉን አቀፍ ተደራሽ እንዲኾንም ዘርፈ ብዙ አጋርነት እና ትብብርን ይጠይቃል ብለዋል።
የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት እና ተዛማጅ የዕድገት እክሎችን በጤናው ሥርዓት እንዲካተቱ በማድረግ አካል ጉዳተኝነትን መከላከል እንደሚገባ ሥራ አሥፈጻሚው አንስተዋል።
የስፔሻሊቲ እና ተሐድሶ ሕክምና አገልግሎቶችን በሁሉም የጤና ሥርዓት እርከን ደረጃ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
በተለይም የሕክምና ሥርዓቱን በማጠናከር ለአካል ጉዳተኞች ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ኢሊባቡር (ዶ.ር) ተናግረዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት ተወካይ ሳሪ ማሉማ (ዶ.ር ) ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የአካል ጉዳተኝነትን እና የአፈጣጠር ችግርን ለመከላከል እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ መኾኑን አንስተዋል።
ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኝነትን እና የአፈጣጠር ችግርን ለመከላከል እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ: ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
