ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቆዩ ግንባታዎችን መልክ የማስያዝ ሥራ እየተሠራ ነው።

55

ደብረማርቆስ: የካቲት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ሕንጻ ሹም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን እና ኀላፊነት መሠረት በዋናነት ከከተማዋ ፕላን ጋር በተጣጣመ መልኩ የግንባታ ፈቃድ መስጠት፣ የግንባታ ጥራትን የመከታተል እና የመቆጣጠር እንዲኹም ግንባታቸው ለተጠናቀቁ ሕንጻዎች የአገልግሎት ፈቃድ የመስጠት ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

የተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ሶሊያና መሐሪ በበጀት ዓመቱ ከ15 ሺህ በላይ የፕላን ስምምነት ለመስጠት ታቅዶ ባለፉት ሰባት ወራት መስፈርቱን አሟልተው ለመጡ ከ2 ሺህ 100 በላይ ለሚኾኑ ባለጉዳዮች የፕላን ስምምነት መስጠት ስለመቻሉ ገልጸዋል።

በሁሉም የግንባታ ደረጃዎች ከ2 ሺህ 200 በላይ ለሚኾኑት ደንበኞች የግንባታ ፈቃድ ተሰጥቷል ብለዋል። በበጀት ዓመቱ ከ1 ሺህ በላይ በኾኑ ግንባታዎች ላይ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራዎች እንደተከናወኑም አብራርተዋል።

የባለጉዳዮችን መጉላላት ለመቀነስ ወደ ለውጥ ተግባራት መገባቱን የገለጹት ኀላፊዋ በአዋጅ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ግንባታዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል።

በተጠሪ ጽሕፈት ቤቱ መረጃን የማጥራት እና የማደራጀት ተግባራት እየተከናወነ መኾኑን ያብራሩት ኀላፊዋ ሕገ ወጥ እና ከደረጃ በታች በኾኑ ግንባታዎች ላይ ከደንብ አስከባሪ አካላት ጋር በመቀናጀት የማስተካከያ ርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

ግንባታቸው ተጀምሮ ለዓመታት ሳይጠናቀቁ የቆዩ ግንባታዎችን መልክ የማስያዝ እና የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ ተጀምሯል ነው ያሉት።

ግንባታቸው ተቋርጦ የቆዩ ስድስት የግንባታ ባለቤቶች ወደ ሥራ መግባታቸው የተገለጸ ሲኾን የነባር ግንባታ ባለቤቶች አኹን ላይ በከተማዋ አስቻይ የሰላም ኺኔታ መኖሩን በመገንዘብ ፈጥነው ወደ ግንባታ እንዲገቡም ጥሪ አቅርበዋል።

የመንግሥት የግንባታ ፕሮጀክቶች ተገቢውን ፕላን በማጽደቅ እና መስፈርቶችን አሟልተው ወደ ሥራ በመግባት በኩል ክፍተቶች ስለሚስተዋሉ መታረም እንደሚጠበቅባቸውም ኀላፊዋ አሳስበዋል።

ዘጋቢ፦ ንጉስ ድረስ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሕገ ወጥ መንገድ የተከዘነ 200 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በቁጥጥር ስር ዋለ።
Next articleጥራት ያለው እና ፍትሐዊ የኾነ የሕክምና አገልግሎት መስጠት እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።