
ሰቆጣ: የካቲት 24/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በሁሉም ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳድሮች ለቀበሌ መሪዎች ሥልጠና ተሰጥቷል። የሥልጠናው ተሳታፊዎችም ራሳቸውን የፈተሹበት እና ሕዝባቸውን ለማገልገል ይበልጥ የተነሣሱበት መድረክ መኾኑ ነው የተገለጸው።
ቄስ ስለሺ ደባሽ የሰቆጣ ዙርያ ወረዳ የ04 ቀበሌ ሊቀ መንበር ናቸው። ሥልጠናውን ከመውሰዳቸው በፊት ከልምድ በመነሣት ሕዝቡን ይመሩ እንደነበር አስታውሰው ከሥልጠናው ባገኙት ዕውቀት ግን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን በመለየት ሕዝቡን በእኩልነት ለማገልገል ይበልጥ መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል።
የመንግሥት ሥራ የሚጀምረው ከቀበሌ መኾኑን ያወሱት ቄስ ስለሺ ከቀበሌ ጀምሮ የተጠናከረ ሥራ በመሥራት የለማች እና የተረጋጋች ሀገርን መገንባት እንችላለን ነው ያሉት። ባለፉት ዓመታት በነበረው ጦርነት በሴቶች የሚደርሰው ጥቃት ከፍተኛ እንደነበረ የተናገሩት ደግሞ የሰቆጣ ዙርያ ወረዳ 024 ቀበሌ የሴቶች ጉዳይ ተጠሪ ወይዘሮ ገነት ታፈረ ናቸው።

በቀበሌው ያለው ሰላም የተሻለ ቢኾንም አልፎ አልፎ የሚታዩ ጥቃቶች አሉ የሚሉት ወይዘሮ ገነት ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የተዘጋጀ ቀበሌ ነው ብለዋል። የሰቆጣ ዙርያ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እና አሠልጣኝ መሐመድ ኡመር የሥልጠናው ግብ በአቅም የጎለበቱ እና የሕዝብን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ የሚችሉ መሪዎችን መፍጠር ነው ብለዋል።
ህልም ያለው የቀበሌ መሪ ካለ ቀበሌው ወደ ልማት እና ዕድገት ያመራል፤ ቀበሌ ከለማ ደግሞ ወረዳ እና ዞን እየበለጸገ ይሄዳል ነው ያሉት። የጠነከረ የቀበሌ መዋቅር በመዘርጋት ሰላሟ የተረጋገጠች ሀገርን እንገነባለን የሚሉት አቶ መሐመድ ኡመር እንደ ዙርያ ወረዳም በሁሉም ቀበሌዎች ያሉ ማኅበረሰቦች ከሰላም ጎን በመቆም እየሠሩት ያለው ሥራ የሚበረታታ መኾኑን አውስተዋል።
ይህንን አንጻራዊ ሰላም በማጽናት ሕዝቡን በብስለት እና በዕውቀት የሚመራ የቀበሌ መሪ መፍጠር የሥልጠናው ግብ ነው ያሉት አሠልጣኙ በቀጣይም በሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ማኅበረሰቡን በሥርዓት እና በሕግ የመምራት ኀላፊነት አለባቸው ብለዋል። ለተከታታይ ሦስት ቀናት ሲሰጥ የነበረው የቀበሌ መሪዎች ሥልጠናም ተጠናቅቋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
