
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ መልዕክት በደብረ ታቦር ከተማ እቴጌ ጣይቱ አደባባይ ተክብሯል። በበዓሉ አከባበር ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) “የዓድዋ ድል የነጻነት ጮራ የታየበት ነው” ብለዋል
የአሁኑ ትውልድ በትንንሽ ችግር ሳይበገር በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት መንፈስ እያጋጠሙ ያሉትን ፈተናዎች በማለፍ አንድነትን ማጠናከር አለበት ብለዋል። ሰላምን ማረጋገጥ እና ልማትን ማፋጠን እንዳለበትም ተናግረዋል። የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮንን የዓድዋ ድል በዓል ሀገራችን ኢትዮጵያን ወርሮ የነበረውን የጣሊያን ፋሽስት ሠራዊት ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነትነት እና በቆራጥነት ታግለው ድል የነሱበት ነው ብለዋል። አባቶች ዋጋ ከፍለው ነጻነትን ማስረከባቸውንም ተናግረዋል። ድሉም አውሮፓውያንን ያስደነገጠ እና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ጮራን የፈነጠቀ መኾኑን ገልጸዋል።
ጀግኖች አባቶች እና እናቶች ተናብበው እና ተቀናጅተው ታሪክ ሠርተው ማለፋቸውን የተናገሩት ከንቲባው ወጣቶች ከቀደምት ጀግኖች የተረከቡትን አኩሪ ታሪክ በተገቢው ሁኔታ መጠበቅ እና ማስቀጠል አለባቸው ነው ያሉት። የራሳቸውን ታሪክ ለማስመዝገብም ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት አምባቸው ሞላ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመውጣት ወራሪውን የጠላት ሠራዊት ድል ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የአሁኑ ትውልድ ከጀግኖች አባቶቻችን በመማር የሀገሩን አንድነት ለማስቀጠል በመከባበር እና በመተጋገዝ መሥራት አለበት ነው ያሉት። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየውን አላስፈላጊ ውዝግብ እና ግጭት በማቆም አንድነትን እና የጋራ ጉዞን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎች የዓድዋ ድል ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ ተምሳሌት መኾኑንም ገልጸዋል። ያለምንም ልዩነት በጋራ ኾነን ሀገራችን ለማሳደግ እና ሰላሟን ለማረጋገጥ እንሠራለን ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
