“ዓድዋ ነጻነትን ለሚሹ ሕዝቦች ሁሉ የማይጠፋ የብርሃን ጸዳል ነው” ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ

47

ባሕር ዳር: የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓድዋ ድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ መልዕክት በአዲስ አበባ ተከብሯል። በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የዓድዋ ድል ለአፍሪካ እና ለመላው የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተምሳሌት ኾኖ ተስፋን ያበሰረ፣ ቅኝ ገዢዎች ሊያጠፉት የጣሩትን ሰብዓዊ ክብር መልሶ ያጎናጸፈ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጀግንነት ያሳየ ነው ብለዋል።

ዓድዋ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ እና ብልሃት የገለጠ ድል መኾኑንም ተናግረዋል። የዓድዋን ድል ስናከብር ጎልቶ የሚታየው የኢትዮጵያን ሃሳብ እና ፍልስፍና ነው ብለዋል። የዓድዋ ድልን ስናከብር የድሉ መሠረት እና ምንጭ የኾነውን ሃሳብ በጥልቀት መመርመር ነው፤ ገድሉን ስንዘክርም ኢትዮጵያውያን ኀያል የተባለውን ሀገር ያሸነፉበት ምስጢሩ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ የማይታለፍ የዘመን ጥያቆ ነው ብለዋል።

ዓድዋ ማለት ትጉህ የኾነ የዕውቀት ኀይል እና የሃሳብ ሙግት መነሻ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ዓድዋ ልሒቅነት ያለው፣ ብሩሕነት ያለው፣ የሃሳብ መነጋገሪያ እና ማዳወሪያ ነው ብለዋል። “ዓድዋ የአንድ ወቅት ድል ብቻ ሳይኾን ትናንትን የወሰነ፣ የበየነ፣ ዛሬን የገለጠ፣ ነገን የተለመ የታሪክ ሀብል፣ የማይበጠስ ብርቱ ሰንሰለት ነው” ይላሉ።

ኢትዮጵያውያን ያልተቆራረጠ ሥርዓተ መንግሥት ያለን፣ አንድንትን መሠረት ያደረግን ነን ብለዋል። ሕልውናችንን ለማስቀጠል የነበረንን ዝግጁነት፣ ኢትዮጵያውያን ለነጻነት የምንሰጠው ፋይዳ እና ዋጋ ከፍ ያለ መኾኑ ለዓድዋ ድል አብቅቶናል ነው ያሉት። እናንተ ታላቅ ብርቱዎች ተነሱ፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ተገልጣለችና ተብሎ መጻፉን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ በዓድዋ ለአፍሪካውያን የተገለጠች መኾኑን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያዊነት በነጻነት እና በሰውነት የማመን የእምነት መገለጫ መኾኑንም ገልጸዋል። ኢትዮጵያን ማፍቀር እና መውደድ፣ ለኢትዮጵያ ራስን ፈጽሞ መስጠት ምንጊዜም የሃሳብ እቶን እና የማይበርድ የመንፈስ ሙቀት መኾኑን አሳይተውናል ነው ያሉት። ይህ መንፈስ ቀድሞም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ነገም የሚኖር ነው ብለዋል።

የዓድዋ ድል የበርካታ ጉዳዮች ኅብር መኾኑንም ተናግረዋል። “ዓድዋ ነጻነትን ለሚሹ ሕዝቦች ሁሉ የማይጠፋ የብርሃን ጸዳል ነው” ብለዋል። ከዓድዋ የምንወስደው ታላቅ በረከት ሀገር ከግላዊ ቅሬታዎች፣ ከፖለቲካ በላይ መኾኑን ነው ይላሉ ፕሬዝዳንቱ። ኢትዮጵያን ማዕከል በማድረግ በእኩልነት፣ በነጻነት እና በእድገት መዘመን መቻል አለብን ብለዋል። ኢትዮጵያዊነትን ያገዘፈው የዓድዋ ድል በአርዓያነቱ ታላቅ መኾኑንም ተናግረዋል።

ዓድዋ ጽንፍ አመለካከትን፣ መንደርተኝነትን፣ ቀበሌኝነትን የናቀና የተጠየፈ ሃሳብ መኾኑንም አንስተዋል። በዘረኝነት ስልባቦት ያልተጋረደ መኾኑን ተናግረዋል። ዓድዋ በታላቅ ተጋድሎ የተገኘ ጸጋ እና በረከት ነው ብለዋል። ነጻነትን ዋጅቶ ድህነትን መልበስ፣ እኩልነትን ተናግሮ ለልመና ከሰው ደጃፍ መቆም ለኢትዮጵያ ታሪክ ተስማሚ አለመኾኑም አንስተዋል። “ነጻነት በዕድገት ይደምቃል፣ በመበልጸግም ይዋባል፣ ራስን በመቻልም ይደረጃል” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ስለዚህ የዓድዋን ድል ስናከብር፣ ረሃብን ከእነሰንኮፉ በማስወገድ እና ልመናን በማስቀረት መኾን አለበት ነው ያሉት።

ትናንት የነበረው፣ ዛሬም ያለው ነገም የሚኖረው ኢትዮጵያዊነት በተግባር እንዲገለጥ በርትተን እንሥራ ብለዋል። የድህንነት ካባን ከላያችን አሽቀንጥረን ለመጣል የጀመርነውን ሁለገብ የልማት እርምጃ አጽንተን እንያዝ፣ መድኅናችን እርሱ ነው፣ ቀጣይነታችን እርሱ ነው፣ የኢትዮጵያ የዕድገት ብርሃን ሲደምቅ ሊንቁን የሚፈልጉ፣ ሊጫኑን የሚጣደፉ በትርምስ የተካኑ እና የሠለጠኑ ሁሉ ባሕሪያቸውን ይገራሉ፣ መስተጋብራቸውንም ያሳምራሉ ነው ያሉት።

በዕድገት መትጋት የዚህ ዘመን ትውልድ ኀላፊነት እና አደራ ነው ብለዋል። የዓድዋን እሳቤ ያነገበ የመከላከያ ኀይል ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል። ይሄ እንዲኾን እያደረጉት ላለው ሥራ ምስጋና አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ወጣት ለሀገሩ ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካ የሚተጋ እንደሚኾን አልጠራጠርም ነው ያሉት።

ትውልዱ በእኛ ባልኾኑ ደራሽ እና የአፍታ ወጎች ሳይወሰድ፣ ኢትዮጵያዊ እሳቤን በማጽናት ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል። ዓድዋ ለፓን አፍሪካኒዝም ውልደት እና ቀጣይ ዕደገት የቸረውን በረከት ለመግለጥ ራሱን የቻለ የአፍሪካ ጥናት እና ምርምር መገንባት ይጠበቃል ነው ያሉት። የዓድዋ ድልን ከነድምቀቱ እናክብርም ብለዋል በመልዕክታቸው።

በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዓድዋ ድል በዓል በጎንደር ከተማ እየተከበረ ነው።
Next article“የዓድዋ ድል የነጻነት ጮራ የታየበት ነው” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)