
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የሙሉዓለም ባሕል ማዕከል 129ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በባሕር ዳር ከተማ አክብሯል። የባሕል ቡድኑ የዓድዋ ድልን የሚዘክሩ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን አቅርቧል።
በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የሙሉዓለም ባሕል ማዕከል ዳይሬክተር ገብረማርያም ይርጋ በበዓሉ ባደረጉት ንግግር የዓድዋ ድል የነጭ የበላይነት አስተሳሰብ የሟሸሸበት እና የጥቁር ሕዝቦች አልበገር ባይነት የተመሰከረበት መኾኑን በማስታወስ ይህንኑ ጀግንነት ለማስቀጠል መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዓድዋ ድል ትላንት የጥቁርን ሕዝብ ጨዋነት እና መደማመጥ አስመስክረናል ያሉት ዳይሬክተሩ ዛሬ ደግሞ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀውን አስቦ የዘመኑን ዓድዋ መሥራት ያስፈልጋልም ብለዋል። የኋላውን ሳንተው ታሪካችን እየዘከርን ሌላ ታሪክ መሥራትም ይጠበቅብናል ነው ያሉት። አባት አርበኛ አያና ተገኘ የዓድዋ ድል ታሪክ በተለያዩ በዓሎች መዘከሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። የጥንት አርበኞች በእግር ወጥተው ወርደው ሀገር ማስከበራቸውን ጠቅሰው የአሁኑ ትውልድ ደግሞ የአባቶቹን ታሪክ እንዲያስቀጥል ጠይቀዋል።
ድህነትን በፍቅር እና በአንድነት ለማጥፋት ትኩረት እንዲሰጥም አሳስበዋል። ሃምሳ አለቃ ተስፋው ሙሉ በበኩላቸው አባቶቻቸው ዘምተው ሀገር ማስከበራቸውን ተናግረው የአባቶቻቸውን አርበኝነት ሁልጊዜ እንደሚዘክሩ አብራርተዋል። አሁንም የሀገር አንድነት እና ሉዓላዊነት እንዲከበር በዓሉ በየዓመቱ መከበሩ ተገቢ እንደኾነ ነው ያስረዱት።

የዓድዋ ድል የተገኘው በትልቅ ትግል ነው፤ የአሁኑ ትውልድም ሳይዘናጋ ሀገሩን መጠበቅ አለበት ነው ያሉት። ወጣት ሀብታሙ በሪሁን ዓድዋ የአንድነት እና የመቻቻል ድል ስለኾነ የአሁኑ ትውልድም የዓድዋውን ዘመን መከተል እንደሚገባው ነው የገለጸው። ጠንክሮ በመሥራት ድህነትን ማሸነፍ ይገባልም ነው ያለው።
የዓድዋን በዓል ስናከብር ጥቁሮች ዘመናዊ ነጭን ያሸነፉበት እንደኾነ በማሰብ መኾኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት ዳግም ግርማ ነው። የዘመኑ ትውልድ ደግሞ አንድነቱን ጠብቆ እርስ በእርስ በመመካከር ያለበትን ችግር መፍታት እና ሌላ የዓድዋ ታሪክ መሥራት ይገባዋል ብሏል። ወጣት ኤልሳቤት አድማሱ ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የድል በዓል እና ኩራት መኾኑን ገልጻለች። የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ከድህነት ለመውጣት ሥራ ሳይንቅ መሥራት እና የሀገሩን ነገር አጥብቆ መያዝ እንዳለበት አሳስባለች።
ባሕልን ጠብቆ በመያዝ እና የሀገሩን ማንነት ማስቀጠል እንዳለበትም ገልጻለች።
ዘጋቢ ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
