“ኢትዮጵያ በማንኛውም ኀይል አትሸነፍም” ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

77

ባሕር ዳር: የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የዓድዋ የድል በዓል “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ መልዕክት በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው። በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በቅኝ ገዢዎች ወራሪ ሠራዊት እና በኢትዮጵያውያን አርበኞች መካከል ዓደዋ ላይ የተደረገው ጦርነት በኢትዮጵያውያን ጀግኖች አሸናፊነት በመጠናቀቁ በመላው ዓለም አፍሪካውያን አሸነፉ የሚል ዜና የተሰማበት ነው ብለዋል።

ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቆጣጠር ያሰማሩት የወራሪ ሠራዊታቸው ሽንፈት ለዓለም ሕዝብ የተለየ ዜና እንደነበር ነው ያስታወሱት። ዜናውን ለማመን ተቸግረው እንደ ነበር እና ክስተቱ መርዶ ኾኖባቸው እንደ ነበር ገልጸዋል። የቅኝ ግዛት ዓላማ አራማጆች ሃዘን ላይ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል ነው ያሉት።

በዓድዋ ድል ቅኝ ገዢዎች ሁሉም የሰው ልጅ እኩል መኾኑን እንዲመረምሩ ተገድደዋል ብለዋል። የኢትዮጵያውያን ድል በቅኝ ተገዢነት እና በባርነት ቀንበር ሥር በነበረቡት ጥቁር ሕዝቦች ከፍተኛ ደስታ እንደፈጠርም ገልጸዋል። በቅኝ ግዛት የተያዙት ሁሉ ለነጻነት የሚያደርጉትን ትግል እንዲያቀጣጥሉ አነሳስቷል ነው ያሉት።

የዓድዋ ድል የአፍሪካን ሕዝቦች በቅኝ ግዛት ለመግዛት የተነሳሳ ሁሉ በጥቁር ሊሸነፍ እንደሚችል ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል። በጥቁር ሕዝቦች ዘንድ ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜት እንዲዳብር ማድረጉን ነው የተናገሩት። የዓድዋ ድል የበርሊንን የቅኝ ግዛት እኩይ እቅድ እንዲከሽፍ ያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል የቅኝ ግዛትን ሕልምን ያከሸፈ እና ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለመላው አፍሪካውያን የድል ቀንዲል እንዲለኮስ ያደረገ ነው ብለዋል። በዓድዋ ድል የኢትዮጵያን አሸናፊነት የወራሪውን ተሸናፊነት ያረጋገጠ ውል እንዲፈረም ያደረገ መኾኑንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ ዛሬም፣ ወደፊትም ጠላቶቿን እያንበረከከች ሉዓላዊነቷን በበላይነት የምትቋጭ ሀገር መኾኗን ለጠላትም ለወዳጅም ማስገንዘብ እንፈልጋለን ነው ያሉት። ከዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ በዓለም ፊት እንድትከበር ኾናለች ብለዋል።

የዓድዋ ጀግኖች ልጆች እና የልጅ ልጆች በዓድዋ ድል ብንኮራበት ተገቢ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ መኩራት ብቻ በቂ አይደለም የአባቶቻችንን የአሸናፊነት እና የአይበገሬነት መንፈስ ወርሰን፣ ለድል ያበቃቸውን መንገድ ተከትለን በመጓዝ የሀገራችን ክብር አስጠብቀን ማስቀመጥ አለብን ነው ያሉት።

የዓድዋ ጀግኖች ቅኝ ገዥነትን እና ባርነትን ተጸይፈው ክብራቸውን እና ነጻነታቸውን ላለማሳደፈር ከጠላት ጋር መተናነቃቸውንም ተናግረዋል። የሀገር ነጻነት እና ሰላም አደጋ ላይ ሲወድቅ በጹኑ የአንድነት መንፈስ በመቆም የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበርን የዓድዋ ታሪክ ይነግረናል ብለዋል። ባለንበት ዘመን የሀገርን ጥቅም ለመጉዳት ከሚመጣ ጠላት ጋር መቆም የኢትዮጵያን ታሪክ አይደለም ነው ያሉት።

ባንዳነት ሀገርን ዋጋ እንደሚያስከፍልም ተናግረዋል። ዛሬም ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ተልዕኮ የሚቀበሉ አሉ ነው ያሉት። እኛ ኢትዮጵያውያን ደከሙ ሲሉን ጠንክረን የምንወጣ፣ ተሸነፉ ሲሉን በወኔ እና በእልህ ድል የምንጎናጸፍ ጀግኖች ነን ብለዋል። እኛ ኢትዮጵያውያን ክፉ ቀን ሲመጣብን እና ለአደጋ የተጋለጥን በመሰለ ጊዜ የሚከዱን ሁሉ በአሸነፍን ጊዜ ሃፍረትን ይከናነባሉ ነው ያሉት።

ወጀብ በመጣ ቁጥር ኢትዮጵያ ተሸንፋለች ብላችሁ ለጠላቶቻችን ለማጎብደድ ክብራችሁን አትሽጡ ብለዋል። “ኢትዮጵያ በማንኛውም ኀይል አትሸነፍም የዓድዋን ጀግኖች እሴት እና የጀግንነት መንፈስ የወረሰው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ይጠብቃታል” ነው ያሉት። ሠራዊታችን ውስጣዊ አንድነቱ የጠነከረ፣ የሀገር ፍቅር ስሜቱ እጅግ ከፍ ያለ፣ ወታደራዊ ብቃቱ የዳበረ እና ወኔው የጋለ ነው ብለዋል። በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰፋ ያሉ ሥራዎች መሠራታቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ገጥመው ማሸነፍ የማይችሉ ኀይሎች በበሬ ወለደ ወሬ ለማዳከም የሚሠሩ እንዳሉም ተናግረዋል። ጽንፈኞች እና አሸባሪዎች ሕዝብን እንደሚያደናግሩም ገልጸዋል። ሠራዊቱን ለመከፋፈል የሞከሩ ሁሉ አልተሳካለቸውም ነው ያሉት። ፖለቲካ መሥራት ማለት የሀገር መከታን ማፈረስ ማለት አይደለም ብለዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጠላቶቹን ድል እያደረገ የሀገርን ክብር እንደሚጠብቅም ተናግረዋል። ሠራዊቱ በሀገር ላይ የሚቃጣን ጥቃት በሙሉ ብቃት የሚመልስ እና የማይሸነፍ መኾኑን ገልጸዋል። በጫካ ያሉ ኀይሎች አሁን ያለውን ሠራዊት ማሸነፍ እንደማይቸሉ በመረዳት ለሰላም መግባት እንዳለባቸው አሳስበዋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ወትሮው ሁሉ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር እንዲቆም አሳሳስበዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዓድዋ ጀግኖች መንፈስ ሀገሩን እንዲጠብቅም አስገንዝበዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ለዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
Next articleየአሁኑ ትውልድ ተባብሮ ድህነትን በማሸነፍ ዳግም ዓድዋን መሥራት እንዳለበት ተገለጸ።