“የኢትዮጵያውያን ተጋድሎ እና የአሸናፊነት ምስጢር”

18

ባሕር ዳር: የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ ለ2 ሺህ ዓመታት ያህል የተደጋገመ የወረራ ሙከራ እንደተደረገባት የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ። በአውሮፓ፣ በእስያ እና በአፍሪካ የተነሱ መንግሥታት ግዛታቸውን ሲያስፋፉ በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያንም ለማስገበር ብዙ ጊዜ ሞክረዋል።

ኢትዮጵያን ለማስገበር ከተነሱ የአውሮፓ ነገሥታት መካከል የሮማው አውጉስቶስ ቄሳር አንዱ ነው። አውጉስቶስ ቄሳር በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና እስያ የሚገኙ በርካታ ሀገራትን ተቆጣጥሮ ካስገበረ በኋላ “አይሎስ ጋሎስ” በሚባል የጦር አዛዥ አማካይነት የእግረኛ እና ፈረሰኛ ጦር በግብጽ እና በሱዳን በኩል አድርጎ የአክሱምን መንግሥት ለመውጋት ገሰገሰ። ይህንን የሰሙ ኢትዮጵያውያን ቀድመው ተዘጋጅተው ወደ ኢትዮጵያ ሳይገባ ጦርነት ገጠሙት። ለዓመታት በቆየው ውጊያ የቄሳሩ ጦር እየተመናመነ በመምጣቱ የጦር አዛዡ ከሮማው ንጉሥ በታዘዘው መሠረት ጦርነቱ በእርቅ አልቆ የተረፈውን ወደ ሀገሩ ይዞ ተመለሰ። እንግዲህ የጣሊያን ትንኮሳ በዋናነት ከዚህ የጀመረ ይመስላል።

በአውጉስቶስ ቄሳር የደረሰውን ሽንፈት ብድር ለመመለስ በ54 ዓ.ም በሮማ ነግሶ የነበረው ንጉሥ ኔሮ ፎክሮ ተነሳ። የኔሮ አማካሪዎችም ኢትዮጵያውያን በጦርነት የማይሸነፉ መኾናቸውን እና ወደ ኢትዮጵያ ጦር መላክም ትርፉ ውርደት መኾኑን አስጠነቀቁት። ኔሮ የአማካሪዎቹን ምክር ቢሰማም የዓባይን ምንጭ የሚፈልጉ እንደኾኑ አድርጎ የዘመኑን የኢትዮጵያ ጦር የሚሰልል ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ላከ። የተላኩ ሰላዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ከርመው ሲመለሱ ሀገሪቱ እጅግ ለም መኾኗን፣ ሕዝቡ ደግሞ ጦረኛ መኾኑን ወደ ኢትዮጵያ ጦር መላክ እንደማያዋጣ ነገሩት።

የተነገረውን አልሰማ ያለው ኔሮ ኢትዮጵያን ማስገበር እንደሚችል በመተማመን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ድል ተመትቶ መመለሱን የታሪክ ጸሐፊዎቹን “ዲዩ ካሲዮ” እና “ፕሊኒ” ን ጠቅሰው ጳውሎስ ኞኞ የኢትዮጵያ እና የኢጣሊያ ጦርነት በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፍ አስፍረውታል። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ሥምምነት ላይ በደረሱበት ወቅት ጣሊያኖች ሀገራቸውን ወደ ጥንቱ የሮማ አገዛዝ ለመመለስ ተነሱ። ኢጣሊያ ህልሟን ለማሳካት ምቹ ጊዜ ኾኖ ያገኘችው ደግሞ ከቀይ ባሕር – ሕንድ ውቅያኖስ እስከ ዛንዚባር ድረስ ያለው አካባቢ ነበር። በአያቶቻቸው ያልተሳካውን ኢትዮጵያን የማስገበር ሕልም ለማሳካት በሃይማኖት ሰበብ በአባ ጁሴፔ ሳፔቴ አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ከባላባቶች ጋር ተወዳጁ።

በ1862 ዓ.ም ከባላባቶቹ “ለማረፊያ” በሚል መሬት በመግዛት “ሩባቲኖ” የሚባል የኢጣሊያ የመርከብ ኩባንያ ወደብ እንዲመሠርት አደረጉ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩት አጼ ተክለ ጊዮርጊስ ከአጼ ቴዎድሮስ ያልተረጋጋች ሀገር ተረክበው ስለነበር ጉዳዩን ያሰቡበት አይመስልም። ኩባንያው ወደቡን ለ12 ዓመታት ከተጠቀመበት በኋላ በ1874 ዓ.ም (በአጼ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት) ለኢጣሊያ መንግሥት ሸጠው። በዚሁ ዓመት የኢጣሊያ መንግሥት አሰብ የኢጣሊያ ግዛት መኾኗን በአዋጅ አሳወቀ። ከዚህም ባለፈ በምጽዋ ጦር በማስፈር ወደ መሃል ሀገር መስፋፋቱን ቀጠለ። በሁለቱ ሀገራት መካከል መካረሩ እየጠነከረ ሂዶ ዶጋሌ ላይ ድል ተመቱ። በ1888 የሀገሪቱን ድንበር ጥሶ በድጋሜ ወረራ ፈጸመ።

ለመኾኑ ለአድዋ ጦርነት መንስኤ ምን ይኾን?

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ጌትነት ያሳቡ ለ1888 ዓ.ም የዓድዋ ጦርነት መሠረታዊ መንስኤ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት የመያዝ የቆየ ፍላጎት፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ነጻነቷን የማስጠበቅ ነበር። ለጦርነቱ አነሳሽ ምክንያት የኾነው ደግሞ የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ላይ የተቀመጠው የኢጣሊኛ እና የአማርኛ ትርጉም መዛባት እንደኾነ ገልጸዋል።

በወቅቱ ጣሊያኖች ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ እንዲያመቻቸው በአንቀጹ የአማርኛው ትርጉም “ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ለሚኖራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የኢጣሊያን አገልግሎት ልትጠቀም ትችላለች” የሚል ነው። ይህ ደግሞ ሀገሪቱ ለሚኖራት ግንኙነት ንጉሡ ቢፈልግ ይጠቀሙ፣ ባይፈልጉ በወዳጁ ኢጣሊያ በኩል ሊያደርግ እንደሚችል ያስቀመጠ ነው። የኢጣሊያንኛው ትርጉም ደግሞ “ኢትዮጵያ ፈለገችም፣ አልፈለገችም ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ለምታደርገው ማንኛውም ዲፕሎማሲያዊም ኾነ የንግድ ግንኙነት በኢጣሊያን መንግሥት በኩል እና አጋዥነት ማድረግ አለባት” የሚል አስገዳጅ ሥምምነትን ያስቀመጠ እንደኾነ ነው የገለጹት። ይህም ሀገሪቱን በኢጣሊያ ሥር የጣለ፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ነጻነት የሚጋፋ ኾኖ በመገኘቱ አጼ ምኒልክ እንደማይቀበሉት መናገራቸውን ተከትሎ ጦርነቱ አይቀሬ ኾነ።
ኢጣሊያ ዘመናዊ ሠራዊት አሰልጥና፣ ዘመኑ ያፈራውን የጦር መሳሪያ ታጥቃ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ሥር ለማድረግ ወረራ ፈጸመች።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ ገረመው እስከዚያ (ዶ.ር) እንዳሉት በዓድዋ ጦርነት ወቅት ኢጣሊያ 52 መድፎችን የታጠቀ 20 ሺህ ዘመናዊ ሠራዊት አሰለፈች። የታጠቀችው መድፍም “የተራራ መድፍ” የሚባለው ርቀት ያለን ቦታ መምታት የሚችል ነበር።

አጼ ምኒልክ ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ፍላጎት ቀድመው በመረዳታቸው የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ከራሷ ከኢጣሊያ ጨምሮ ከተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ቀድመው ሸምተው ነበር። በወረራው ወቅትም ከኢጣሊያ ሠራዊት ከ5 እጥፍ የሚበልጥ፣ ትጥቅ እና ስንቅ በራሱ የኾነ የገበሬ ጦር ተሰለፈ። ሠራዊቱ 42 መድፎችም የታጠቀ እንደነበር ገልጸዋል።

በዓድዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት በኢትዮጵያ በኩል ብዙዎች ቆሰሉ፤ በርካቶች ደግሞ ሕይዎታቸውን አጥተዋል። በኢጣሊያ በኩል ደግሞ ጀነራል አሪሞንዲ እና ዳቦር ሜዳ ዓድዋ ላይ ሕይዎታቸው ሲያልፍ የኋላ ደጀን የነበረው ጀኔራል ኤለና ወደ ኋላ ሸሽቷል። ጀኔራል አልቤርቶኒ እና በርካታ መኮንኖችም ተማርከው አዲስ አበባ ከቆዩ በኋላ በሁለቱ ሀገራት ሥምምነት መሠረት ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።

ኢትዮጵያውያን አድዋ ላይ ያሸነፉበት ሚስጢርስ ምን ይኾን?

የመልካዓ ምድራዊ አቀማመጡ ለጠላት ባዕዳ መኾኑ፣ ተልዕኮ የተሠጣቸው ኢትዮጵያውያን ሰላዮች የማሳሳት አቅም፣ ጦርነቱ ለኢትዮጵያውያን ፍትሃዊ መኾኑ፣ የመሪዎች የመሪነት ጥበብ፣ የሕዝቡ ሀገር ወዳድነት ኢትዮጵያ ጦርነቱን በበላይነት እንድታጠናቅቅ ምክንያቶች መኾናቸውን ዶክተር ገረመው ጠቅሰዋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ጌትነት ያሳቡ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ቁርጠኝነት፣ አይበገሬነት፣ የሀገር ፍቅር፣ አንድነት፣ ለንጉሡ የነበራቸው ታማኝነት፣ ወኔ እና ጀግንነት ለድሉ በምክንያትነት አስቀምጠዋል።

ሌላኛው በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ትምህርት መምህር መላኩ ጌቴ እንዳሉት ደግሞ ጀነራል ባራቴሪ የኢትዮጵያን የጦር አቅም አሳንሶ ማየቱ፣ የኢትዮጵያ ሰራዊት የተከፋፈለ፣ ከንጉሡ ጋር ያለመግባባቶች እንዳሉ መረዳቱ እንዲሁም ጦሩ የተሰላቸ፣ የሎጀስቲክስ ችግር እንዳጋጠመው በማመኑ ዓድዋ ላይ ድል ለመደረጉ ምክንያቶች እንደኾኑ አስቀምጠዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዓድዋ ድል በዓል በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ተከበረ።
Next article“የዓድዋ ድል የ19ኛው ክፍለ ዘመን ታላቅ ጦርነት እና ድል ነው” ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው