
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ዓድዋ ምሥራቅ ነው የነጻነት ጀምበር የዘለቀችበት፣ ዓድዋ ምዕራብ ነው የቀኝ ገዢዎች ጀምበር የጠቀለችበት፣ ዓድዋ አለት ነው ነጻነት የጸናበት፣ ዓድዋ የማይነጥፍ ጅረት ነው ትውልድ ሁሉ የነጻነት ውኃን እየጠጣ የሚረካበት፣ ዓድዋ ነጋሪት ነው የኢትዮጵያ ከፍታ የሚጎሰምበት፣ ዓድዋ አዋጅ ነው የአንድነት ቃል የሚነገርበት፣ ዓድዋ መስታውት ነው የጀግኖች ግርማ የሚታይበት፣ ዓድዋ ከተራራዎች ሁሉ የላቀ ተራራ ነው ከፍታ የሚለካበት፣ ዓድዋ የማይበጠስ ገመድ ነው ትውልድ ሁሉ የሚተሳሰርበት፣ ዓድዋ ማሕተም ነው ነጻነት የታተምበት፣ ዓድዋ ብዕር ነው ጀግንነት በደም ቀለም የተጻፈበት፣ ዓድዋ ዙፋን ነው የነጻነት ንጉሥ በግርማ የሚቀመጥበት፣ ዓድዋ ጥበብ ነው የጀግንነት ታሪክ የሚዘመርበት፣ ዓድዋ ሙዚዬም ነው የታላቅ ሕዝብ ታሪክ የሞላበት፡፡
ዓድዋ ፀሐይ ነው ጥቁር ብርሃን ያየበት፡፡ ዓድዋ ሚዛን ነው ሰው እኩል የተለካበት፡፡ ዓድዋ ፍትሕ ነው የእውነት ፍርድ የተገኘበት፡፡ ተበዳይ የተካሰበት፡፡ በዳይ የካሰበት፡፡ ዓድዋ ድልድይ ነው ዓለም ከአንድ ታሪክ ወደሌላ ታሪክ የተሸጋገረበት፡፡ ዓድዋ ረቂቅ መንፈስ ነው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የተሠባሠቡበት፡፡ ዓድዋ የብርሃን በር ነው ጥቁር ሁሉ ከባርነት ወደ ነጻነት የወጣበት፡፡ ዓድዋ መንገድ ነው ጥቁር ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዘበት፡፡
ዓድዋ የማይጠልቅ ጀምበር ነው ነጻነት የሚበራበት፣ ዓድዋ የማያረጅ መንበር ነው የከበረ ንጉሥ ከከበረች ንግሠት ጋር የሚቀመጡበት፣ ክብር እና ኩራት ለዘላለም የሚኖሩበት፡፡ ዓድዋ አጸድ ነው ነጻነት ያለው ሕዝብ ሁሉ የሚሠባሠብበት። ዓድዋ የለመለመ መስክ ነው ተስፋና ተድላ የበቀለበት።
ዓድዋ ጦር ነው ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት፡፡ ዓድዋ ካባ ነው ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሚደርቡበት፣ በፍቅር የሚያጌጡበት፡፡ ዓድዋ የጋራ ቤት ነው ኢትዮጵያውያን በአንድነት የሠሩት፣ በአንድነት ያስጌጡት፣ በአንድነት የሚኖሩበት፣ በአንድነት ለልጆቻቸው የሚያወርሱት፡፡ ክብሩን ጠብቀው የሚያኖሩት፡፡
ዓድዋ ያለው ሁሉም አለው፡፡ ዓድዋ ዓለማት ሁሉ የሚቀኑበት፣ ኃያላን ነን የሚሉ ሁሉ የሚርበደበዱለት፣ ጥበበኛ መሪዎች፣ ከጥበበኛ ሕዝብ ጋር ኾነው የሠሩት፣ በደም እና በአጥንት ያቀለሙት ረቂቅ ታሪክ ነው፡፡ ዓድዋ ኢትዮጵያ በዓለም ታሪክ ደምቃ የተጻፈችበት፣ ኢትዮጵያውያን ወደር በማይገኝለት ጀግንት የደመቁበት፤ የዓለምን አተያይ የቀየሩበት፤ በዓለሙ ፊት ሁሉ በኩራት የሚኖሩበት፣ በክብር የሚወደሱበት ድል ነው፡፡
በዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ታላቅነታቸውን አስመስክረዋል፡፡ በዓድዋ ድል የማትናወጽ ነጻነታቸውን አንጸዋል፡፡ ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ጀግኖች የጀግንነት ልክ የታየበት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ጀግና ከኢትዮጵያውያን ውጭ በየትኝም ሀገር አልተገኘም፡፡ አይገኝምም፡፡ ስለምን ቢሉ ሞትን ንቀው፣ ከጠላት ጋር ተናንቀው ወራሪን አሳፍረው መልሰዋልና፡፡ በዓድዋ በአንድ ጀምበር የዓለም የታሪክ አካሄድ ተቀይሯል፡፡ በአንድ ጀምበር የቅኝ ገዥ ቅስም ተሰብሯል፡፡ የቅኝ ገዥ ሕልም ቅዠት ኾኗል፡፡ በአንድ ጀምበር የጣሊያን ክብር ላይነሳ ተቀብሯል፡፡ በአንድ ጀምበር የኢትዮጵያ ዝና ማንም ላያወርደው ከፍ ብሎ ተሰቅሏል፡፡ በአንድ ጀምበር ወደር የሌለው ታሪክ ተሠርቷል፡፡ በአንድ ጀምበር ከጦርነቶች ሁሉ የላቀው ጦርነት ተካሂዷል።
ዓድዋ ላይ ያጋሱት ጀግኖች የገደሉት ዓድዋ ላይ የመጡትን የጣሊያን ወታደሮችን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቅስ በአውሮፓ ኾነው ለቅኝ ግዛት ሲዘጋጁ የነበሩ ነገሥታትንም ጭምር እንጂ፡፡ እንደምን ኾኖ ቢሉ ብዙዎች በዓድዋ ድል ዕቅዶቻቸውን ትተዋል፡፡ የቅኝ ግዛት ሕልማቸውን ረስተዋል፡፡ በኢትዮጵያውያን ጀግንነት ደንግጠዋል፡፡ ቀኝ የመግዛት ወኔያቸው ሞቷልና፡፡
ኤሜረተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1847 እስከ 1983 ዓ.ም በተሰኘው መጽሐፋቸው በዓድዋ ጦርነት ያልተሳተፈ የኢትዮጵያ ክፍል አልነበረም ይላሉ፡፡ የምኒልክ ጦር በቁጥሩ ብዛት ብቻ ሳይኾን ድፍን ኢትዮጵያን የወከለ በመኾኑም ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ነበር፡፡
ለንጉሠ ነገሥቱ ነጻነት እና የሀገር ድንበርን የማስከበር ጥሪ ጦር ያልላከ የሀገሪቱ ክፍል አልነበረም ነው የሚሉት። ለዛም ነው ዓድዋ የአንድነት ውጤት ነው የሚባለው።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የዓድዋ ድል በተሰኘው መጽሐፋቸው ስለ ዓድዋው ጦርነት ሲጽፉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ወታደሩ አርሶ አደሩ እና ነጋዴውም ካህናቱ ሳይቀሩ ስለ ሀገራቸው ነጻነት ስለ ንጉሣቸው ክብር ሲሉ ሞታቸውን የማይፈሩ ጀግኖች እና ቆራጦች ናቸው እና የመድፉን እና የጠመንጃውን ተኩስ ሳይፈሩ በሠልፉ ውስጥ ገቡበት፡፡
የፊተኛው ሲወድቅ የኋለኛው ወደፊት ከመገስገስ በቀር የወደቀውን ላንሳ ደክሞኛል እና ልረፍ አይልም ነበር፡፡ እቴጌ ጣይቱ አይዞህ በርታ ይሉት ነበር፡፡ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስም ወደጦርነቱ የሚገባውን ወታደር እግዚአብሔር ይፍታሕ ይሉ ነበር፡፡ የጦርነቱም አኳኋን አለቃውም ጭፍራውም ፍየል እንዳየ ነብር በየፊቱ ከመሮጥ ከመግደል በቀር በአንድነት ቆሞ ለመዋጋት አያስብም ነበር፡፡ እንኳን የጭፍራ አለቆች ደጅአዝማቾች እና ራሶችም ቢኾኑ በፈረስ እየኾኑ አንደኛውን እየጋለቡ ይገድሉ ነበር፡፡
በጠመንጃ መግደል ከጉብዝና ስላልቆጠሩት በጎራዴ ለመግደል ይሽቀዳደሙ ነበር፡፡ ይልቁንም ተራ ወታደር ከመግደል ይልቅ የጦር አለቆችን መግደል ጀግንነት ነው እያሉ ተራውን ወታደር እያለፉ በቆቡ እና በልብሱ የወርቅ ምልክት ያለበትን የጦር አለቃ ይፈልጉ ነበር ብለው ጽፈዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ከልባቸው ጀግኖች ናቸው የሚባሉት በምክንያት ነው። ጀግንነታቸው ከዓለሙ ሁሉ የላቀ እና የረቀቀ ነውና።
በዚህ ጀግንነት የተዋጉ ጀግኖች በአንድ ጀምበር ጠላትን ድባቅ መቱት፡፡ የማይደፈሩ መኾናቸውን አሳዩት፡፡ በአንድ ጀምበር የዘላለም ደማቅ ታሪክ ጻፉ፡፡ በምኒልክ የአዋጅ ጥሪ የተሠባሥበው፣ በጀግኖች የጦር መሪዎች የሚመራው ከኢትዮጵያ ከአራቱም አቅጣጫ የተሠባሠበው የኢትዮጵያ ጦር በሀገር ፍቅር ስሜት ተዋግቶ፣ በሀገር ፍቅር ድል ነስቶ የማይጠፋ አሻራ አተመ፡፡ ቅኝ ለመግዛት የመጣውን እንዳልነበር አድርጎ መለሰ፡፡ ነጭን ሁሉ አሳፈረ፡፡ በአማረ ቤተ መንግሥት ተቀምጠው አፍሪካውያን ቅኝ ለመግዛት ሲያሴሩ የነበሩ ነገሥታት ሁሉ ፍርሐት ወረሳቸው። የቅኝ ግዛቱን ሐሳብ ትተው ከኢትዮጵያ ወዳጅነት ለመፍጠር ተቻኮሉ።
ኤሜረተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ሲጽፉ በትልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ይዋጋ የነበረው የኢትዮጵያ ጦር በስልት እና በቅንጅትም ከጠላት ልቆ በመገኘቱ ምንም እንኳ ብዙ ሰው ቢያልቅም በጠላት ላይ የማያወላውል ድል ተቀዳጀ፡፡ እኩለ ቀን ላይ ጦርነቱ አከተመ፡፡ የኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ ሕልም ዓድዋ ሜዳ ላይ ሲቀበር ኢትዮጵያ በነጻነት መኖሯ ተረጋገጠ ብለዋል፡፡
እንደ ዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዝናን የሰጡ ድርጊቶች ማሰብ ያዳግታል፡፡ የቅኝ አገዛዝን ማዕበል የገታ አንድ ትልቅ ድርጊት እንደመኾኑ ሁሉ የቅኝ ገዢዎችን ቅስም የሰበረውን ያህል የተገዢዎቹን አንገት ደግሞ ቀና እንዲል ያደረገ ክስተት ነበር፡፡ በዚህ ድል ምክንያትም የፖለቲካ መሪዎችም ኾኑ ነጋዴዎች አቋማቸውን እንደገና እንዲመረምሩ ተገደዱ ብለው ጽፈዋል፡፡
በዓድዋ ድል ኢትዮጵያ የነጻነት እና የክብር ፋና ኾነች፡፡ ቀድሞውንም ቢኾን በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የምትታወሰው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያኒዝም እየተባለ ለሚጠራ ከነጮች ተጽዕኖ ነጻ የኾነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ መንስኤ ኾና ነበር፡፡ በዓድዋ ድል ቀድሞ በረቂቁ ትታወቅ የነበረችው ኢትዮጵያ ሥጋና ደም ተላብሳ ታየች ነው የሚሉት ኤሜረተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ።
ሐሪ አትክንስ የኢትዮጵያ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው የዓድዋ ድል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛውን ደረጃ የያዘ ድርጊት ከመኾኑ በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለው የቆዬ የነጻነት ፍቅር አርማ ሊኾን በቅቷል ብለዋል፡፡ ጣሊያኖችም የውጫሌ ውል መደምደሚያ የኾነውን ኢትዮጵያ አንድ ታላቅ ነጻ ሀገርነቷን በማወቅ ከኢትዮጵያ ጋር የሰላም ውል ተዋዋሉ፡፡
ታላቁ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያን በዓለም ካርታ ላይ ከማጉላቱ ጋር በቀላል በቅኝ ግዛት ሥር ለመኾን የማትበገር አፍሪካዊት ሀገር በማለት አውሮፓውያን የሥራ እና የዲፕሎማቲክ መልዕክተኞቻቸውን በመላክ ከንጉሥ ምኒልክ ጋር ውል መፈራረም ጀመሩ ብለው መዝግበዋል፡፡ የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ገናና እና የከበረ ድል ነው፡፡ ይህ ድል ለኢትዮጵያውያን ረቂቅ እና ድንቅ ነው፡፡ ስለምን ቢሉ ማንም ያልፈጸመውን ገድል ፈጽመውበታል፣ ማንም ያልሠራውን ታሪክ ሠርተውበታል፡፡ ማንም ያላደረገውን አድርገውበታልና፡፡
እነኾ ትውልድ ሁሉ እየኮራበት፣ እየተመካበት ይኖራል።
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!