
ባሕር ዳር: የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በዚህ ሳምንት ለሚከበረው የአደዋ ድል በዓል እንደመነሻ ኾኖ ይጠቀሳል የውጫሌ ውል። ይህ ውል በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል በ1881 ዓ.ም ነበር የተፈረመው። በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይህ ክስተት ዋና ዓላማው የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት መደበኛ ማድረግ እና የድንበር ጉዳዮችን መፍታት ነበር።
ነገር ግን በውሉ ውስጥ የተካተቱት አንቀጾች በተለይም የአንቀጽ 17 ትርጉም ላይ በተፈጠረው ልዩነት ምክንያት ለከፍተኛ አለመግባባት እና በመጨረሻም ለዓድዋ ጦርነት ምክንያት ኾኗል። የውጫሌን ውል በ1881 ዓ.ም በውጫሌ ከተማ በኢትዮጵያ በኩል ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ እና በጣሊያን በኩል ፒዬትሮ አንቶኔሊ ናቸው የፈረሙት።
በዚህ ውል ላይ አንቀጽ 17 በውሉ ውስጥ ትልቅ አለመግባባት የፈጠረ ነበር። በጣሊያንኛ ቋንቋ ትርጉም ኢትዮጵያ ከሌሎች የውጭ ሀገራት ጋር የምታደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያን በኩል ብቻ እንድታደርግ ይደነግጋል። በአማርኛ ትርጉም ግን ኢትዮጵያ ከሌሎች የውጭ ሀገራት ጋር በጣሊያን በኩል ማድረግ እንደምትችል እንጂ ግዴታ እንዳልኾነ ይገልጻል።
ይህ የትርጉም ልዩነት ጣሊያን ኢትዮጵያን በጠቅላይ ግዛትነት ለመቆጣጠር እንደምትፈልግ በግልጽ ያሳየ ነበር። ይህን ውል እንደማይቀበሉት የገለጹት ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ የጣሊያንን የጠቅላይ ግዛትነት ሙከራ በመቃወም ለዓድዋ ጦርነት መዘጋጀት ግድ ኾኖባቸዋል። የዓድዋ ድል በዓል በኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ታሪካዊ ክስተት ነው። ይህ በዓል የኢትዮጵያውያን ጀግንነት፣ አንድነት እና ለነፃነታቸው የነበራቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
የዓድዋ ጦርነት በ1888 ዓ.ም በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል የተደረገ ሲኾን ኢትዮጵያውያን በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ መሪነት ጣሊያኖችን ድል ያደረጉበት ታሪካዊ ጦርነት ነው። ይህ ድል ለአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት ኾኖ የሚታወስ ሲኾን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ክብር ያሳየ ነው።
በዓድዋ ድል በዓል ላይ ኢትዮጵያውያን የጀግኖቻቸውን ገድል በማስታወስ ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር እና ታማኝነት ያድሳሉ። በዓሉ የተለያዩ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ዝግጅቶች የሚካሄዱበት ነው። የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለመላው አፍሪካ ትልቅ ትርጉም ያለው ድል ነው። ይህ ድል አፍሪካውያን ለነፃነታቸው መታገል እንደሚችሉ እና አንድነት ሲኖራቸው ማንኛውንም ፈተና መቋቋም እንደሚችሉ ያሳየ ነው።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የዓድዋ ጦርነት ተካሄደ። በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ፣ በንግሥት ጣይቱ ብጡል እና በሌሎች የጦር መሪነት ኢትዮጵያውያን ጣሊያኖችን ድል አደረጉ። ይህም ድል ለሀገሪቱ መልካም ነገርን ይዞ ብቅ አለ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ነፃነትም ከፍ ማድረግ የቻለ ነበር።
የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን መተባበር እና አንድነትን ማውረሱን፣ ኢትዮጵያን በዓለም ላይ የነጻነት ተምሳሌት ማድረጉን እና የኢትዮጵያዊያንን የአስተሳሰብ ልዕልና ያሳየ አጋጣሚም ነው። ይህም የኾነው የካቲት 23 በዚህ ሳምንት ነበር።
✍️ ተጽዕኖ ፈጣሪው አዋጅ!
የደርግ መንግሥት እንደ አውሮፖውያን አቆጣጠር 1975 ያወጣው አዋጅ ቁጥር 31 የመንግሥት ሠራተኞች እና ሌሎች ዜጎች የፖለቲካ ትምህርት እንዲወስዱ ያስገደደ ነበር። ይህም አዋጅ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ኹኔታ ምክንያት ወሳኝ ቦታ የሚሰጠው ነበር። አዋጁ በወቅቱ የነበረውን የሶሻሊስት አስተሳሰብ በሕዝቡ ዘንድ ለማስረጽ እና ለማስፋፋት ያለመ ነበር።
የሕዝቡን የፖለቲካ ግንዛቤ ለማሳደግ እና ለደርግ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ታማኝ ዜጎችን ለመፍጠር ያለመ ነበር። የደርግ መንግሥት በሕዝቡ ላይ ያለውን ቁጥጥር ለማጠናከር ታሳቢ አድርጎም ይህን አዋጅ እንዳወጣ ይገለጻል። አዋጁ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች፣ የከተማ ነዋሪዎች እና ሌሎች ዜጎች የፖለቲካ ትምህርት እንዲወስዱ ያስገደደ ነበር።
ትምህርቱ የማርክሲዝም-ሌኒኒዝም ርዕዮተ ዓለምን፣ የደርግ መንግሥትን ዓላማዎች እና ፖሊሲዎችን ያካትት ነበር። የፖለቲካ ትምህርቱን ያልወሰዱ ዜጎች የተለያዩ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽኖዎች ይደርስባቸው እንደነበርም መረጃዎች ያሳያሉ። አዋጁ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥ ከፍተኛ ተፅዕኖ ነበረው።
የፖለቲካ ትምህርቱ በብዙ ዜጎች ዘንድ ተቀባይነትን ያጣና የደርግ መንግሥት ላይም ከፍተኛ ተቃውሞዎች እንዲነሱ ምክንያት እንደነበረ ታሪኩ ያስረዳል። የደርግ መንግሥት የፖለቲካ አስተሳሰብን በሕዝቡ ላይ በግድ ለማስረጽ መሞከሩ ለተለያዩ የፖለቲካ ችግሮች እና ግጭቶች እንደዳረገውም ነው የሚነገረው። አፍሪካን ሎው አርካይቨን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።
✍️ ለነጻነት የተደረገው ጥረት!
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1951 በፊት ግብጻውያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ነበራቸው። አድራጊ ፈጣሪም ነበሩ ማለት ይቻላል። ይህ ክስተት ከእስክንድርያ ተሹመው የሚመጡ ፓትርያርኮች ከቤተክርስቲያኗም አልፈው በሀገሪቱ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ በማሳረፍ በኢትዮጵያውያን ላይ የነፃነት መንፈግ ሁኔታዎችም ይስተዋሉ ነበር።
ይህንን ነጻነት ለማስመለስ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። በ20ኛው ክፍለ ዘመን ታዲያ ኢትዮጵያውያን የቤተ ክርስቲያናቸውን ነፃነት ለማስከበር ከፍተኛ ጥረት አደረጉ። ይህ ጥረት በንጉሠ ነገሥት ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል። በተደረገው የነጻነት ትግል በዚህ ሳምንት በ1943 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከእስክንድርያ ፓትርያርክነት ነፃ መውጣትም ችላለች።
በዚያው ዓመት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ተሹመዋል። ይህ ታሪካዊ ክስተት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሉዓላዊነትን ያረጋገጠ ትልቅ ምዕራፍ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ጉዳዮች በራሷ እንድታሥተዳድር ያስቻለ ክስተትም ኾኖ አልፏል። ይህ ክስተት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውም ነው።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!