
ባሕር ዳር፡ የካቲት 23/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” ከዛሬ 129 ዓመት በፊት ያስነገሩት የክተት አዋጅ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ከማሰባሰብ እስከ ድል አድራጊነት በስኬት የታጀበ ወርቃማው ታሪካችን ነው።
“ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ፤ ሀገር አስፍቶ አኖረኝ። እኔም እስካሁን በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። እንግዲህም ብሞት ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ ልዑል እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠረጥረውም። አሁንም ሀገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት ልዑል እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል። እኔም የሀገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመረ።
አሁን ግን በልዑል እግዚአብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም። የሀገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልኩህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። አሁንም ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህና ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘን እርዳኝ። ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም፤ እግዝዕትነ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይኢሉ ከተህ ላግኝህ” ይላል የምኒልክ አዋጅ።
ከወደዚያ ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት መለከት ያሰማ፣ የባርነት ሰንሰለትን እንዲበጣጥሱ ያነሳሳ፣ ፋናውም ከአጽናፍ አጽናፍ ያበራ ነው፣ የምኒልክ አዋጅ፡፡ አውሮፓውያን በአፍሪካ ያላቸውን የበላይነት ወኔ የሰበረ ነው፣ የምኒልክ አዋጅ። ከወደዚህ ደግሞ ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ፣ ሕዝባቸውን የሚያከብሩ፣ ጠብን እየተጠየፉ ሰላምን የሚያሰፉ ምኒልክ የሚባሉ የሐበሻ ንጉሥ አሉ፡፡ በብዙው ታግሰው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ቢያደርጉም የኢትዮጵያውያን የነጻነት ቀንዲልነት ይታደስ በዓለም ፖለቲካ እና የቅኝ ግዛት ታሪክ የመጨረሻው መጀመሪያ ይኾን ዘንድ ጣሊያን ኢትዮጵያን በይፋ ወረረች፤ ንጉሠ ነገሥቱም ክተት አወጁ፡፡
አዋጁ የንጉሡን የሕዝብ አመራር ጥበብ፣ የተቀባይነት ደረጃ፣ በዙፋናቸው እና በሕዝባቸው መተማመንን፣ ያመላከተ እንደነበር ነው ምሁራን የሚናገሩት፡፡
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝም እና ቅርስ አሥተዳደር መምህር እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪ ቀሲስ እርጥባን ደመወዝ የ1888 ዓ.ም የአጼ ምኒልክ የክተት አዋጅን አንደምታ አብራርተውልናል፡፡ የአዋጁ ይዘት እና ውጤቱ የአጼ ምኒልክን የአመራር ጥበብ ማመላከቻነት አብራርተውልናል፡፡ በግዕዝ ቋንቋ “ምኒልክ ማለት የአዋቂ ልጅ ማለት ነው” ያሉት ቀሲስ እርጥባን አጼ ምኒልክ የአባቶቻቸውን ጥበብ እየተማሩ ያደጉ ጥበብንም ሀብት ያደረጉ፣ ሕዝብን ያሻገሩ፣ ለትውልድ የተረፉ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጥበባቸው አንዱ መገለጫው የትናንቱንም የነገውንም የሚያይ መነጽራዊ መኾኑን ጠቅሰዋል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ለእንግሊዞች፣ አጼ ዮሐንስ ለደርቡሾች እጅ ያለመስጠት ታሪክ መድገማቸውን እና የቀጣዩ ትውልድ እንዳያፍር ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
አጼ ምኒልክ ገዢውን እና ሕዝቡን የሚያስተሳስር አመራር ተከትለዋል፡፡ ሕዝቡን እና በጊዜው የነበሩትን ምሁራን የእነ አጽመ ጊዮርጊስ፣ እነ ዮሴፍ፣ እነ አፈወርቅ ገብረኢየሱስን ምክር ይሰሙ ነበር። ከጣሊያን ጋር የውጫሌው ሥምምነት አንቀጽ 17 ጉዳት ሐሳብ ያቀረቡት አፈወርቅ ገብረኢየሱስ እንደነበሩም ጠቅሰዋል፡፡ የየቦታውን ራሶች እነ ራስ አሉላ፣ ራስ ሀጎስ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ ጉግሳ ወሌንም ያካተተ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
አጼ ምኒልክ ችግርን ያጠና እና ፈዋሽ የአሥተዳር ጥበብ ይከተሉ እንደነበር እና የቀደምቶቻቸውን መስዋዕት አስቀጥሎ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያሻግር ነበር፡፡ መሪ የሚባለው የሕዝቡንም የወቅቱንም ኹኔታ ተረድቶ ማሥተዳደር የሚችል ነው ያሉት ቀሲ እርጥባን ንጉሠ ነገሥቱ ኢትዮጵያ እንድትዘምን እና አፍሪካን ነጻ አውጥታ ለዓለም ያስተማረችው ባለ ራዕይ መሪ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
ጣሊያን ኢትዮጵያን እንደወረረች በታወቀ ጊዜ ሕዝቡ ለነጻነቱ እንዲዘምት የጠሩበት አጭር ግን ሰፊ ሐሳብ ያለውን አዋጅ አብራርተውልናል፡፡ በቀሲስ እርጥባን ምሁራዊ ትንታኔ መሰረት፡- “ሞዓ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዳግማዊ ምኒልክ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ” ማለት ከምኒልክ የተላከ መልዕክት ማለት ነው፡፡ በወቅቱ አጠቃቀም እግዚአብሔር ከሾመኝ፤ ንግሥናን ከአባቶቼ ከነገሥታት የተቀበልኩ ከምሆን፤ ንግሥናየም አንበሳዊ ከኾነ፣ ከሣህለ ሥላሴ ልጅ ከኔ ከሁለተኛው ምኒልክ የተላከ ማለትንም ይወክላል፡፡
“ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ፤ ሀገር አስፍቶ አኖረኝ…” ሲሉም የሾማቸው እግዚአብሔር እንደኾነ እና ሕዝቡም እንደሚያውቅ ጠቅሰው በኃይላቸው እንዳልተመኩ እና ሀገር የሁሉም መኾኗን አመላክለተውበታል ብለዋል፡፡ “እኔም እስካሁን በልዑል እግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ።” ሲሉም የፈጣሪያቸውን ረዳትነት አስታውሰዋል፡፡ ሰው የሆነ ሁሉ እንደሚሞት፣ ቀደምት ነገሥታትም ሞተዋል እኔም እሞታለሁ በማለት ታሪክ ሠርቶ የማለፍን አስፈላጊነት ሲያስታውሱ ደግሞ “እንግዲህ ብሞት ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም።” የማለታቸውን ምስጢር ዘርዝረዋል፡፡ እናንተ ሂዱ እኔ ልቅር አለማለታቸውንም አንስተዋል፡፡ ሠርተው የሚያሠሩ እንጂ እናንተ ተዋጉ እኔ ልቅር አለማለታቸው ነው ብለዋል፡፡
“ደግሞ ልዑል እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም። ከእንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠረጥረውም።” ሲሉ ፈጣሪ በውጪ ከመገዛት ነጻ እንዳደረጋቸው አስታውሰው ሕዝቡንም በሀገሩ፣ በአምላኩ፣ በአባቶቹ፣ የትህትና ጥሪ ሲያደርጉለት ነው፡፡ “አሁንም ሀገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል።” በማለት የመጣባቸው ጠላት ሌላ ባሕል፣ ታሪክ እና ሃይማኖት ያለው መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ ጠላት ብለው የጠቀሷቸው ግብጾች፣ ቱርኮች፣ እንግሊዞች፣ ጣሊያኖች እና መሐዲስቶችን ነበር፡፡ ስለዚህ ጠላት ሲመጣ ታሪክን እና እሴትንም እንደሚያጠፋ ነው የገለጹት፡፡
በወቅቱ ሀገሩ በድርቅ እና በከብት በሽታ የተመታበት ስለነበር ይህንኑ መረዳታቸውን ለማመላከትም “እኔም የሀገሬን ከብት ማለቅ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው…’ ማለታቸውን ገልጸዋል፡፡ ድካማችሁን የከብቶቻችሁንም ማለቅ እገነዘባለሁ፤ ነገር ግን ጠላት ከሁሉም በምትበልጠው በሀገራችን እና ነጻነታችን የመጣ ነው፡፡ ሀብት ንብረት አልቆብኛል ብለህ ባትከላከለው የቀረህን የሚቀማ፣ ባርያ አድርጎ ይገዛኻል ማለታቸው ነው፡፡
“… ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር።” ሲሉ ሥልጣኔ አስተማሪ በመምሰል ባሕል፣ ቋንቋ፣ ሥነ ልቦና ሥሪትን አጥንተው ለወረራ መምጣታቸውን ማመላከታቸው ነው። ወዳጅ መስለው እንደመጡ ስላወቁ ነው በፍልፈል የመሰሏቸው። የገዢ አንዱ ትልቅነቱ የወዳጅ እና ጠላትን ሥነ ልቦና መለየት መኾኑንም አክለዋል፡፡
“አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት ሀገሬን አሳልፌ አልሰጠውም።” ማለት እግዚአብሔርን የሚለምኑበት የአዋጅ ደብዳቤ መኾኑን ያመለክታል፡፡ “የሀገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፤ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም።” በማለት ሰው ነኝና ብበድልህ እንኳ ይቅር ትለኛለህ በማለት ከሕዝባቸው ጋር ፍቅር መኾናቸውን አመላክተዋል፡፡
“አሁንም ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ርዳኝ፤ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህ እና ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘን ርዳኝ” ማለታቸው ሰው እንደፀጋው በጦርነቱ መሳተፍ እንዳለበት በትህትና እየነገሩት መኾኑን እንገነዘባለን፡፡ “ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፤ አልተውህም፤” ማለታቸው ደግሞ ርምጃ እወስዳለሁ ነው፡፡ ከትህትናቸው እና ከእውነተኝነታቸው በተጨማሪ የገዢ፤ የአንበሳ አመልንም ያሳያሉ፡፡ ዘምቶ ጠላትን ከማሸነፍ እና ቀርቶ እንደጠላት ከመቆጠር ሌላ አማራጭ እንደሌለም ነው በአዋጃቸው የገለጹት፡፡ ትቀጣለህ ከጠላት ወገን ትመደባለህ ነው ያሉት፡፡ አስቀድሞ መንገርም ነው፡፡ ትጣላኛለህ ሲሉም መጣላት በኋላ ይተረጎማል፤ ‘ይህንን አደርግኻለሁ’ ሲሉ ንጉሥን የተጣላ ምን እንደሚደርስበት በኋላ የሚታይ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
“እግዝዕትነ ማርያምን! ለዚህ አማላጅ የለኝም።” በማለት ጠላትን ሲዋጉ ያላገዛቸውን በብርቱው እንደሚጣሉት አስቀድመው ያሳወቁት በእምነቱ፤ በእምነታቸው ነው፡፡ “ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና፤ የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።” አጼ ምኒልክ ጊዜ፣ ቦታ፣ ሁኔታ ገልጠው ነው በአዋጃቸው ጥሪ ያደረጉት ብለዋል፡፡ ዙፋናቸው ሸዋ ላይ በመኾኑ ቅድሚያ የተቀመጡበትን አካባቢ ሸዋን ጠቅሰዋል፡፡ የየግዛቱን ንጉሦች በቀጣይ መጥራታቸውንም አስታውሰዋል፡፡
ቀሲስ እርጥባን ማንም የቀረ የማይመስልበት የአድዋው ጦርነት በዓል ነው የኾነው፡፡ ቄሱ ታቦት ተሸክሞ፣ ወጣቱ በጉልበቱ እና በዱላ፣ ሴቶች በምግብ ማዘጋጀት፣ የቆሰለውን በማከም እና በማበረታታት፣ መሳተፋቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የዚያን ዘመን የአመራር ጥበብ በክተት አዋጁ ለማሳየት ሞከርን እንጂ በሌሎች የሀገር አሥተዳደር ጥበብ የሚስተዋል ነበር፡፡ የእቴጌ ጣይቱ ብልህነት እና ምክር በኋላም በጦርነቱ ስልት እና ስትራቴጅም የማይዘነጋ እንደኾነ ነው የምንመለከተው።
አጼ ምኒልክ ‘እምዬ’ የሚለው ቅጽላቸው ከርህራሄያቸው በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር እና ምጥ በድል ስላዋለዱ የተሰጣቸው የአክብሮት ሥም መኾኑ ይነገራል፡፡ ”ምኒልክ ተነስቶ ባያነሳ ጋሻ ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ ሐበሻ” የተባለውም በአዋጁ፣ በዘመቻው እና በተገኘው የነጻነት ድል ነው። በአጼ ምኒልክ እና መንግሥታቸው የአመራር ጥበብ የምናከብረው በዓል የማሸነፍ እንጂ ነጻ የመውጣት አለመኾኑን ቀሲስ እርጥባን አስገንዝበዋል፡፡
ዛሬም መሪም ኾነ ተመሪ የበርሊንን አጀንዳ ተረድተን ታሪካችንን አውቀን ለከፋፍለህ ግዛ መመቸት የለብንም። ሀገርን አንድ በሚያደርግ ነገር ላይ ማተኮር አለብን። የቀደምቶቻችን ታሪክ ማክበር ለተደረገልን ነገርም ማመስገን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!