”ለሴቶች ተጠቃሚነት ትላንትን ሳይኾን ነገን እያሰብን መሥራት ይገባል” ወይዘሮ ብርቱካን ሲሳይ

39

ባሕር ዳር: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በሴቶች አመራር ፎረም የክልሉ ሴቶች ሁለንተናዊ ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ስለሚረጋገጥበት ኹኔታ ውይይት ተደርጓል። ችግሮች ተነስተው የመፍትሄ ሃሳቦችም ተመላክተውበታል።
ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ሁሉን አቀፍ ንቅናቄ መጀመሩ ተነስቷል።

የፎረሙ ተሳታፊ ወይዘሮ ማስተዋል አለባቸው የሴቶች ፎረም መድረክ ሴቶችን ወደ ኀላፊነት እንዲመጡ አርዓያ እንደኾነ ገልጸዋል። በርካታ ወጣት እና ምሁራን ሴቶች ለገጠሯ እና ከተሜዋ ሴት ከጫና በመውጣት እንዲሠሩ ይመክራልም ብለዋል።

ሴት መሪዎችን ወደ ውሳኔ ሰጭነት የማምጣትን ሂደትን በማጠናከር ሴቶች የበለጠ ተሳታፊ እንዲኾኑ ነው እየተወያየን ያለነው ብለዋል።

ፎረሙ ተተኪ መሪዎችን በመያዝ ሴቶች ወደ ኀላፊነት እንዲመጡ እና የሴቶችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት እንዲያሳድጉ እያመቻቸ መኾኑንም ገልጸዋል።

የዘንድሮውን ማርች 8 ከሴቶች በመቅረብ ችግራቸውን ለመረዳት እና ለመቅረፍ በመረዳዳት የመሥራት አቅጣጫ መያዙንም ገልጸዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ምክትል ኀላፊ ገቢያ ተስፋ ፎረሙ የሴቶችን የመሪነት ሚና የሚያሳድጉበት መኾኑን ጠቅሰዋል።

ሴቶች ወደ መሪነት ሲመጡ የግማሹን ማኅበረሰብ ክፍል ተጠቃሚነት ማምጣት መኾኑን የጠቀሱት ወይዘሮ ገቢያ የሴቶችን የመሪነት ሚና በማሳደግ የምጣኔ ሃብት እና የማኅበራዊ ችግሮቻቸውን መፍታት መኾኑን ገልጸዋል።

እየተተገበረ ያለውን የሌማት ትሩፋት ጨምሮ አማራጭ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በመሥራት ተጠቃሚ እንዲኾኑ ፎረሙ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

የሴቶች አመራር ፎረም ተቋቁሞ ምክክር መደረጉ ለሴቶች ሁለንተናዊ ለውጥ እና ተጠቃሚነት ትልቅ አስተውጽኦ እንዳለውም ገልጸዋል።

ከሴት አመራሮች ፎረም ቀጥሎም እስከ ቀበሌ በመድረስ የንቅናቄ መድረኮችን በማስቀጠል የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

በአማራ ብልጽግና ፓርቲ የሴቶች ክንፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ኢሌኒ ዓባይ የተደረገው ውይይት ከሴቶች አኳያ በክልሉ የሚሠሩ ሥራዎች እና ለውጦች መኖራቸውን ያመላከተ መኾኑንም ገልጸዋል።

ሴቶች ሥራ አይችሉም የሚል የለም ያሉት ወይዘሮ ኢሌኒ ለመንግሥትም ለፓርቲም ቅርብ ኾነው ኀላፊነታቸውን በመወጣት በኩል የሴቶችን ጠንካራነት ተናግረዋል።

ሴቶችን ወደ ኀላፊነት ለማውጣት መፈታት ያለባቸው ችግሮችም መኖራቸውን ጠቅሰው በዋናነት ሴቶች ራሳቸው መታገል እንደሚገባቸው ነው ወይዘሮ ኢሌኒ የተናገሩት። ሴቶችን የማጠናከር ሥራም እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ሴቶች በብዛታቸው እና በመብታቸው ልክ ይጠቀሙ ዘንድ ለመሥራት እንዲቻል ፎረሙ መቋቋሙን አብራርተዋል። ሴቶች በፖለቲካ አመራር ተሳታፊ እንዲኾኑ እና የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ ለመሥራት መቋቋሙንም ጠቅሰዋል።

ፎረሙ ከተመሠረተ በኋላ የሴቶች ውሳኔ ሰጭነት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው በምጣኔ ሃብት ዘርፍም ሴቶች እያደጉ ነው ብለዋል።

በውይይቱም ሴቶች እርስ በእርሳቸው መደጋገፍ እና ለበለጠ ተጠቃሚነት የተቀመጡ አሠራሮችን መተግበር እንደሚገባቸው አይተናል ብለዋል።

ሴቶች መሥራት እና መወሰን እንደሚችሉ አንስተው እድሉን ማግኘት እንደሚገባቸው ገልጸዋል። ሴቶችን ወደ ኀላፊነት የማምጣት ሥራ ከትላንት እያነጻጸርን ሳይኾን ነገን እያሰብን መሥራት ይገባልም ነው ያሉት።

ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጠንካራ የቀበሌ መዋቅር ካለ ጠንካራ ሀገር መፍጠር ይቻላል”
Next article” አባቶቻችን በዘመናት ርዝማኔ የማይደበዝዝ ታላቅ ድል አስመዝግበዋል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ