
ባሕር ዳር: የካቲት 22:2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ቀበሌዎችን በማፅናት ሁለንተናዊ እምርታን እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ አሥተዳደር ብልፅግና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ለቀበሌ መሪዎች የተዘጋጀ ሥልጠና ተጀመሯል።
በሥልጠናው ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ይፋዊ ንግግር ያደረጉት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ “ሥልጠናው ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ ከሕዝባችን ጋር በሙሉ ነፃነት ውይይት የጀመርንበት፣ ከዛሬ 129 ዓመት በፊት በአድዋ የድል በዓል ዋዜማ ላይ ኾነን የምናስኬደው የብሩህ ተስፋ ጎህ ቀዳጅ መድረክ ነው” ብለዋል።
ብርሃን ዘ-ኢትዮጵያ የሚል ስያሜ ያገኙት ጠበብቷ ንግሥት፣ የጦር መሐንዲስ እቴጌ ጣይቱ ብጡል የተወለዱበት ምድር ላይ ኾነን ይህን መድረክ ስናስኬድ በከፍተኛ ተስፋ እና ብሩህ ዘመን መግቢያ ምዕራፍ ላይ ኾነን ነው ብለዋል ዋና አሥተዳዳሪው።
ሥራችንን በቀጣይ እስከ ታችኛው የሥልጣን እርከን ድረስ እግር የመትከል እና ሰላምን የማጽናት ሥራችን በጀግናው እና ሰላም ወዳዱ ሕዝባችን ሙሉ ድጋፍ ይሳካልም ብለዋል።
የፋርጣ ወረዳ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ጌትነት ይህ መድረክ በአድዋ የድል በዓል ዋዜማ ላይ ኹነን የምናከብረው ስለኾነ ታሪካዊ መድረክ ነው ብለዋል።
የጀመርናቸውን ሰፋፊ ሥራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል ቀበሌዎችን የማጽናት ሥራ እንሠራለን ብለዋል። ሥልጠናውም የተጀመረውን ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ዳር ማድረስ የሚያስችል አቅም የሚፈጥር ሲሉ ተናግረዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ “በክልላችን በሁሉም ቀበሌዎች የሚሰጠው ሥልጠና ክልላችን ገጥሞት ከነበረው ውስብስብ ችግር እየወጣ ስለኾነ በራሱ አቅም የሕግ ማስከበር የበላይነቱን በመያዝ ልማትን ለማሳለጥ የሚያስችል በመኾኑ ነው” ብለዋል።
መንግሥት በአንድ ወገን ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥት የሰላም በሮች ክፍት ናቸው ብለዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!