
ከሚሴ: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባቲ ወረዳ ለቀበሌ መሪዎች “ቀበሌዎቻችንን በማጽናት ሁለንተናዊ ዕምርታ እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት ለሦስት ቀናት የሚቆይ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
ሥልጠናው በጸጥታ፣ በፖለቲካ፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ዙሪያ ያተኮረ ሲኾን፣ የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ያቀረቡት የቪዲዮ ሥልጠናን ጨምሮ የተለያዩ ተዛማጅ የትምህርት ሰነዶች ቀርበዋል።
የወረዳው ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ እና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኀላፊ አህመድ ሙህዲን የሥልጠናውን ሰነድ ሲያስተዋውቁ ከዚህ ቀደም የተካሄደውን የፓርቲ ጉባኤ በማስታወስ የሥልጠናውን ዓላማ እና ዋና ጭብጥ አብራርተዋል።
የባቲ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መሀመድ አብዱ የረመዳን ወርን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ካስተላለፉ በኋላ ሥልጠናው በወረዳው የሚገኙ ቀበሌዎች ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የሕዝብን ማኅበራዊ እረፍት ለማስጠበቅ እንዲሁም የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ መኾኑን ገልጸዋል።
የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጤና መምሪያ ኀላፊ ኡስማን አሊ የቀበሌ መሪዎች ሕዝብን በቀጥታ የሚያገኙ እና ለጠንካራ መንግሥት የሕዝብ ይሁንታ የሚያስገኙ በመኾናቸው በየቀበሌው ሰላምን ማስፈን እና ማጽናት አስፈላጊ መኾኑን አስገንዝበዋል።
ሥልጠናው መሪዎችን በሁሉም ዘርፍ አቅማቸውን በመገንባት ተቀባይነት ያላቸው የሥራ ኀላፊዎችን ለመፍጠር ያለመ መኾኑ ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!