
ባሕር ዳር: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የቀበሌ መሪዎች ስልጠና በመሰጠት ላይ ነው። ስልጠናው በባሕር ዳር ከተማም እየተሰጠ ይገኛል።
“ቀበሌዎቻችንን በማጽናት ሁለንተናዊ እምርታ እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት ስልጠናው ለከተማ እና ለገጠር የቀበሌ መሪዎች ነው እየተሰጠ የሚገኘው።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልእክት በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ኾነዋል። በመኾኑም የቀበሌ መሪዎች ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ በርብርብ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
መንግሥት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ አረጋ ለግብርና ግብዓት ከፍተኛ ገንዘብ ድጎማ አድርጓል። ስለኾነም በድጎማ የተገዛው ግብዓት ወደ ተፈለገው ሥፍራ ተጓጉዞ ለተፈለገው ዓላማ ይውል ዘንድ ከመሪዎች ብዙ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ሕዝብን እያማረረ ያለው የኑሮ ውድነትን ችግር ለመቅረፍ ገበያው በሥርዓት መመራት ይገባዋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ነዳጅ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለውና እጥረቱ እንዲከሰት እያደረጉ ያሉትን ሕገ ወጦች እና ስግብግብ ነጋዴዎች አደብ ማስገዛት በዋናነት የመሪዎች የሥራ ድርሻ ነው።
የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ብልጽግና በብዙ መሰዋዕትነት የተወለደ ትልቅ ፓርቲ መኾኑን አስታውሰው ለውጡ ከውስጥም ከውጭም በብልሃት እና በቅንጅት ስለተመራ ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ ስኬቶችን አምጥቷል ነው ያሉት።
አሳታፊ እና ኀብረ ብሔራዊ የኾነው ብልጽግና በችግር እና ተጽዕኖ ውስጥ ኾኖም የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ስኬቶችን አስመዝግቧል ያሉት አቶ ይርጋ ሕግ የማስከበሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መሪዎችን ማሰልጠን ተገቢ ኾኖ ተገኝቷል።
ብልጽግና በተለየ መልኩ የቀበሌ መሪዎች በግምገማ እና ስልጠና ማለፍ አለባቸው ብሎ ያምናል ያሉት አቶ ይርጋ ሲሳይ ስለኾነም የቀበሌ መሪዎች ሥልጠና በክልሉ በሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አሥተዳደሮች እና ቀበሌዎች ተጀምሯል፤ ለተከታታይ ቀናትም ይቆያል።
ከመጀመሪያ ዙር ሥልጠና ግብዓት በመውሰድም ሁለተኛው ዙርም ስልጠና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ይርጋ ተናግረዋል።
በቀበሌ መሪዎች ላይ ያለው የመሪነት ክፍተት በስልጠና ካልተስተካከለ በክልሉ ያለውን የሕግ ማስከበር ሥራ በፍጥነት መቋጨት አይቻልም ብለዋል።
በክልሉ ያለውን ሃብት እና ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀምም የቀበሌ መሪዎች ስልጠና አስፈላጊ መኾኑን ነው አቶ ይርጋ የተናገሩት።
ባሕር ዳር ከተማን እንደምሳሌ ወስደን ብናይ
ምን የሌላት ፀጋ ይኖራል? ያሉት አቶ ይርጋ ለግብርና የሚመች፣ አየሩ ተስማሚ፣ አርሶ አደሩ ታታሪ ነው። በመኾኑም የቀበሌ መሪዎችን በማሰልጠን ፀጋዋን በአግባቡ መጠቀም ያስችላል ነው ያሉት።
በቀጣይ ሦስት ወራት በክልሉ ያልተቋጨውን ሕግ የማስከበር ሥራ ለማጠናቀቅ መንግሥት ዝግጅት አድርጓል ያሉት አቶ ይርጋ ለዚህ ትልቁ አቅም ቀበሌ ላይ ያለው የብልጽግና መዋቅር ነው።
ሕዝቡ ተደራጅቶ መሪዎችን እና ልማቱን እየደገፈ መኾኑን አቶ ይርጋ ጠቁመዋል። በዚህ ሂደትም በቀጣይ ወራትም በክልሉ የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ሥራ ለማጠናቀቅ ይቻላል ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው የባሕር ዳር ከተማን ልማት ለማፋጠን እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት እውነተኛ መሪዎች መኾን ይጠበቅብናል ብለዋል።
ሰላማችንን በበለጠ በማጽናት፤ ልማትን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ያሉት አቶ ጎሹ ባሕር ዳርን በዓለም የቱሪዝም መዳረሻ ውብ፣ ማራኪ፣ ምቹ ለማድረግ መትጋት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከቀበሌ መሪዎች ከፍተኛ ሥራ ይጠበቃል ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን