
ጎንደር: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ቀበሌዎችን በማፅናት ሁለንተናዊ እምርታ እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት ለቀበሌ መሪዎች ሥልጠና በጎንደር ከተማ እየተሰጠ ነው። በጎንደር ከተማ የሚገኙ የቀበሌ መሪዎች የክልል እና የከተማዋ የሥራ ኀላፊዎች በመድረኩ ተሳትፈዋል።
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብርሃኑ ጣምያለው በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ማኅበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና መሰል ችግሮች መፈጠራቸውን አውስተዋል።
ይህንን እና ሌሎችንም በሕዝቡ ዘንድ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት ብልፅግና ፓርቲ እየሠራ ነው ያሉት አቶ ብርሃኑ ውጤታማ የሰላም እና የልማት ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል። ብልፅግና ፓርቲ የሰላም አማራጮችን የሚመርጥ እና በዚህም ጠንካራ አቋም ይዞ እየሠራ መኾኑንም አብራርተዋል።
አሁን ያለውን አንፃራዊ ሰላም እና የልማት ሥራዎች ለማስቀጠል ብሎም የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ሕዝቡ የበኩሉን እንዲወጣ የቀበሌ መሪዎች ሚና ጉልህ መኾኑን አስረድተዋል። የሰላም ፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የቀበሌ አመራሮች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም አሳስበዋል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ መኮንን በጎንደር ከተማ ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። ለቀበሌ አመራሮች የሚሰጠው ሥልጠና መልካም ተግባራትን ለማጠንከር እና እንከኖችን ለመፍታት የሚያስችል ነውም ብለዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊ የቀበሌ መሪዎች በበኩላቸው ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የብሎክ አደረጃጀት ሥራዎች፣ ወጣቶች ለከተማዋ የሰላም ዘብ እንዲኾኑ ማስቻል እና ማኅበረሰቡ የሰላም ባለቤት እንዲኾን ለማስቻል የቅንጅት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።
በቀጣይም ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ከማኅበረሰቡ እና ከባለድሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመሥራት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- ቃልኪዳን ኃይሌ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን