
ሰቆጣ: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 129ኛው የዓድዋ የድል በዓል በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ “አርበኝነት በዘመኑ ትውልድ” በሚል መሪ መልዕክት ተከብሯል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያሥተላለፉት የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ዋና አሥተዳዳሪ ኃይሉ ግርማይ “የዓድዋ ድል የነጻነታችን ዓርማ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደረገ የጀግንነት ማሳያ ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን አባቶች እና እናቶች የንጉሠ ነገሥቱን አዋጅ ተቀብለው በአንድነት ዘምተው ታላቅ ጀብዱ ፈጽመው አልፈዋል ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው በዋግ ኽምራ በኩልም ዋጉ ሹም ጓንጉል ብሩ ከ10 ሺህ በላይ ዘማች ወታደሮችን በመያዝ በአንባላጌ፣ በዓድዋ ተራሮች ታሪክ የማይሽረው ጀብድ ፈጽመዋል ነው ያሉት።
ዛሬም ማንኛውም ሰው በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ ከኾነ የዓድዋን ድል እንደደገመው ይቆጠራል ሲሉም አቶ ኃይሉ ለበዓሉ ተሳታፊዎች አሳስበዋል።
በዓሉን ለማክበር ከተገኙት መካከል የሰላም አስከባሪ ዘማች እና የሰቆጣ ከተማ አባት አርበኞች አባል ሞገስ ይማነብርሃን ዓድዋ ለአፍሪካውያንም ነጻነታቸውን እንዲያገኙ በር የከፈተ የማሸነፍ ወኔን ያቀጣጠለ የድል በዓል ነው ብለዋል።
ወጣቱ ትውልድም ከአባቶቹ ጀግንነትን፣ የዓላማ ጽናትን፣ አደራ መወጣትን ሊማር እንደሚገባው አሳስበዋል።
በባዶ እግራቸው እና በባሕላዊ የጦር መሣሪያ የዘመነውን የጣሊያንን ሠራዊት ያንበረከኩት በአንድነት በመቆማቸው ነው ያለው ደግሞ የበዓሉ ተሳታፊ ወጣት ሙሉቀን ታድጎ ነው።
ወጣቶችም አባቶች ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው ያጸኗትን ሀገር ከከፋፋይ አጀንዳ በመውጣት ሰላሟን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የማሥተላለፍ ኀላፊነት አለብን ብሏል።
ሌላኛዋ አሥተያየት ሰጭ ተማሪ ሩሔ ኃይሉ ሀገርን ለመረከብ የሀገርን ታሪክ ማወቅ ያስፈልጋልና የዓድዋ ድል በየዓመቱ መከበሩ አባቶች የከፈሉትን ዋጋ ለማወቅ የሚያግዝ ነው ብላለች።
129ኛው የዓድዋ የድል በዓልን በማስመልከት የዳሰሳ ጥናቶች፣ ጭውውቶች፣ ግጥሞች እና ሙዚቃዊ ተውኔቶች በመድረኩ ቀርበዋል።
በበዓሉም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ መሪዎች፣ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዎች፣ አባት አርበኞች፣ መምህራን እና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።
ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!