“ትውልድን ለማሻገር ከቀበሌ ጀምሮ የመሪዎችን አቅም ማጎልበት አስፈላጊ ነው” የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር

14

ደብረ ማርቆስ: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ቀበሌዎቻችንን በማጽናት ሁለንተናዊ ብልጽግና እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት ከደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ለተውጣጡ የቀበሌ መሪዎች ሥልጠና መሰጠት ተጀምሯል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት “ቀበሌዎቻችንን በማጽናት ሁለንተናዊ ብልጽግና እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት ከከተማው ከአራቱም ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ የቀበሌ መሪዎች ሥልጠና መስጠት ተጀምሯል።

የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተሾመ ዋለ ሀገርን በማጽናት ትውልድን ለማሻገር ከቀበሌ ጀምሮ የመሪዎችን አቅም በማጎልበት ጽኑ መሠረት መጣል አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ቀበሌዎች ከፍተኛ የሕዝብ ኀላፊነት ያለባቸው ትልቅ መዋቅር መኾናቸውን በመገንዘብ ሊሠራ የሚችል ጠንካራ መሪ መፍጠር ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል።

ሀገርን ለማሻገር የፓርቲውን ዓላማ በማስረጽ ጠንካራ ተቋም መገንባት አለብን ያሉት ከንቲባው የሕዝብ ጥያቄዎችን አዳምጦ ተገቢ ምላሽ ሊሰጥ የሚችል ብቁ አመራር ኾኖ መገኘት አስፈላጊ መኾኑን ጠቁመዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ባሕል ግንባታ ዘርፍ አማካሪ ዶክተር መስፍን አበጀ መንግሥት የመሪዎችን የመፈፀም እና የማስፈፀም አቅም ለመገንባት እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ቀበሌዎች ለሀገር ግንባታ ወሳኝ የኾኑ የልማት እና የዴሞክራሲ ሥራዎች መሠረት የሚጣልባቸው መዋቅር መኾናቸውን በመገንዘብ የሥራ ኀላፊዎች በዛሬ ፈተና አልፈው ለነገ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሥልጠናው ከአራቱም ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ የቀበሌ የሥራ ኀላፊዎች እየተሰጠ ይገኛል። ሥልጠናው ለተከታታይ ሦስት ቀናት እንደሚቆይ ከመርሐ ግብሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአማራ ክልል መሪነትን በአግባቡ የሚወጣ የቀበሌ መሪ ለመፍጠር ያለመ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
Next articleበክህሎት እና በአስተሳሰብ የተቀራረበ የቀበሌ መሪ አፈጻጸም እንዲኖር እየተሠራ ነው።