
ከሚሴ: የካቲት 22/2017 (አሚኮ) በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የደዋጨፋ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ”ቀበሌዎቻችንን በማፅናት ሁለንተናዊ እምርታ እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት በወረዳው ለሚገኙ የቀበሌ አመራሮች ሥልጠና መሰጠት ተጀምሯል።
በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ ጠንካራ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሥራችን የሚሳካው በቀበሌዎቻችን ጠንካራ መዋቅር መፍጠር ስንችል ነው በሚል በኹሉም አካባቢ ያለውን የቀበሌ መዋቅር ለማጠናከር ታስቦ የተዘጋጀ ሥልጠና ነው ብለዋል።
የሕዝቦች የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች የሚመለሱት በጠንካራ የቀበሌ መዋቅር በመኾኑ ሠልጣኞች በሥልጠናው ያገኙትን እውቀት በመጠቀም የመፈፀም አቅማቸውን በማጎልበት በቀጣይ ሊሠሩ እንደሚገባ አስረድተዋል።
በቀጣይ የልማት፣ የሰላምና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች የርብርብ ማዕከል ቀበሌ ላይ በማድረግ ለሕዝብ ተጠቃሚነት ለመሥራት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ዋና አሥተዳዳሪው ገልጸዋል።
የደዋጨፋ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መሐመድ ጌታቸው ተገልጋይና አገልጋይ በቀጥታ የሚገናኙበት መዋቅር ቀበሌ መኾኑን ጠቅሰው ቀበሌ ላይ መሥራት ሀገር ላይ መሥራት ነው በሚል ሥልጠናው እየተሰጠ ነው ብለዋል።
ወረዳው ባሉት ሁሉም ቀበሌዎች ላይ እግር በመትከል የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም አስገንዝበዋል።
በሥልጠናው የተሳተፉ የቀበሌ አመራሮች በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ቀበሌን የትኩረት ማዕከል በማድረግ ሥልጠና በመስጠቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል። በቀጣይ በሥልጠናው በሚያገኙት እውቀት በመጠቀም ለመሥራት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን