“የዓድዋ ድል በኢትዮጵያዊነት ወኔ የተቀዳጁት የክቡር አክሊል እና ለብሔራዊ ትርክት መሠረት የጣለ የአብሮነት መንፈስ ነው” አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

35

ባሕር ዳር: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንኳን ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በመልዕክታቸው “የዓድዋ ድል በኅብረ ብሔራዊ አንድነት የተገኘ ታላቅ ፍሬ፣ በኢትዮጵያዊነት ወኔ የተቀዳጁት የክቡር አክሊል እና ለብሔራዊ ትርክት መሠረት የጣለ የአብሮነት መንፈስ ነው” ብለውታል።

የዓድዋ ድል ለአንድ ዓላማ በጽናት እና በአብሮነት የመቆም ውጤት ነው ያሉት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ኢትዮጵያዊያን በሀገራዊ አንድነት የማይደራደሩ፣ ላመኑበት ነገር ግንባራቸውን የማያጥፉ እና ፊታቸውን የማይመልሱ መኾናቸውን በገሀድ ያሳየ የአንድነታችን በዓል ነው ብለዋል።

የዓድዋ ድል መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ መደማመጥን እና ብሔራዊ ስሜትን የሚያስተምር ታላቅ ተቋም ነውም ብለውታል።

ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በባሕል፣ በቋንቋ እና በአመለካከት ሊለያዩ ይችላሉ፤ ኾኖም በአንድ እንዲተሙ የሚያደርግ ብሔራዊ የአብሮነት እሴት አላቸው። ይህ ብሔራዊ የአብሮነት እሴት ትናንት በአባቶቻችን ዘመን በዓድዋ ተራሮች አናት ላይ ገዝፎ እና ነፍስ ዘርቶ እንደ አጥቢያ ኮከብ የደመቀ የድል ሰንደቅ ሰቅሏል ነው ያሉት።

ዓድዋ በቅኝ ግዛት ለሚማቅቁት የዓለም ጥቁር ሕዝቦችም “እምቢ ለነጻነት” የሚል ወኔ ሰንቋል፤ ዛሬ በእኛ ዘመን ደግሞ በጉባ ሰንሰላታማ ተራሮች ግርጌ ለብዙዎች መብራት እና ራት የሚኾን ግዙፍ የታሪክ አሻራ የሚኾን ግድብ ገንብቷል፤ ለተፋሰሱ ሀገራትም የ“ይቻላል” መንፈስ ፈጥሯል፡፡

በመኾኑም በዘመናት መካከል ፈተናዎችን በድል የተሻገረውን እና ለቀሪው ዓለም ትምህርት እየሰጠ የመጣውን መልካም የአብሮነት እሴታችንን ልንከባከበው እና ልንጠብቀው፤ ልንኮራበት እና ልንኖረው፣ ለቀጣዩ ትውልድም ሳንሸራርፍ ከነክብሩ፣ ሳናጎድል ከነሁለመናው ልናሸጋግረው ይገባል ብለዋል።

የዓድዋ ድል በዘመኑ የተዛባውን የዓለም ፖለቲካ ሚዛን ለማስተካከል ለሚደረገው ትግል የጥሪ ደወል ኾኖ አነቃቅቷል ያሉት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ነጮች በጥቁሮች ላይ የገነቡትን የኃያልነት እና የበላይነት ትርክት ከመሠረቱ ንዷል፡፡

በአንጻሩ በድንግዝግዝ ጨለማ ውስጥ የሚኖሩ የጥቁር ሕዝቦችን ዐይነ ሞራ ገልጧል፤ የጎበጠውንም ወገባቸውን አቃንቷል፡፡ ወደ ነጻነት የሚመራ የብርሐን ቀንዲል ኾኖ አብርቷል፡፡ ወኔ ኾኖ መነቃቃትን ፈጥሯል፡፡

የዘንድሮውን በዓል “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል” በሚል መሪ ሃሳብ ስናከብርም ከፊት ለፊታችን የታጠሩብንን እንቅፋት የሆኑብንን ከፋፋይ ነጠላ ትርክቶች በምክክር በማፍረስ፣ ኅብረብሔራዊ አንድነትችንን በመግባባት ላይ ለመገንባት ልክ እንደ ዓድዋው ድል በውይይት ችግሮቻችን ለመፍታት በይቅርታ ዘላቂ ሰላምን ማምጣት መቻላችንን ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡

የዓድዋ ድል የጥንት ሥልጣኔ እና የገናና ስም ባለቤት የነበረችውን ኢትዮጵያ ከዘመናዊ ዓለም ጋር መልሶ ያገናኘ ድልድይ ነው። ወድቆ እና ደቆ መቅረት እንጂ ወድቆ መነሳት እና ፈርሶ መሠራት መጥፎ ልንለው የሚገባ አይደለም፡፡ በዛሬ አቅም እንጂ በትናንት ስም አይኖርም፡፡ የጥንቱን ሥልጣኔያችንን እና የትናንቱን ዓድዋችንን በታሪክ ድርሳናት ውስጥ ሕያው ሆነው እንዲቀጥሉ ዛሬያችንን በሁሉም መስክ ማሳመር ይኖርብናል፡፡ የዛሬ አቅም ለነገ ስም፣ የዛሬ ጥረት ለነገ ጥሪት ነውና ብለዋል።

በድጋሚ ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንኳን ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ።

አገኘሁ ተሻገር

የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጥበበኞች ተጋድሎ በዓድዋ!
Next articleቀበሌዎችን የሰላም እና የልማት ማዕከል ለማድረግ እየሠራ መኾኑን የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ገለጸ።