
ባሕር ዳር: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የጥንት አዝማሪዎች ዘፋኝ፣ ማሲንቆ እና ክራር ተጫዋች፣ ታሪክ ተራኪ፣ ፖለቲካዊ አስተያየት ሰጪ እና ታዛቢ ኾነው ያገለግሉ ነበር።
አዝማሪዎች ባላቸው ተሰጥኦ እና ጥበብ በነገሥታቱም ተፈላጊ ነበሩ። በተለየ ኹኔታ ነገሥታቱን እና መኳንንቱን ያዝናኑ እንደነበርም ይነገራል።
አዝማሪዎች እያዋዙ ከማዝናናት ባለፈ ባሕልን እና ወግን በማሳደግ እና የኅብረተሰቡን ይኹን የነገሥታቱን ሕጸጾች ነቅሶ በማውጣት ሚናቸው የጎላ ነበር።
ከዚህም ባለፈ በተለያዩ ጊዜያት ሀገር አደጋ ላይ በወደቀች ጊዜ ጦሩን በማበረታታት እና በማጀገን ሠራዊቱ ለድል እንዲበቃ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በኢጣሊያ ወረራ ወቅት የሠሩትን ጀብዱ ማንሳት ይቻላል።
በዓድዋ ጦርነት ወቅት ከተሰለፉት አዝማሪዎች ውስጥ ስመጥሯ አዝማሪ ጣዲቄ አንዷ ናት። አዝማሪ ጣዲቄ በጦር ሜዳ አርበኞን በማነሳሳት ለሀገራቸው ነጻነት በጀግንነት እንዲፋለሙ አድርጋለች። ጣሊያኖች ለጊዜ መግዣ እና ለማታለያ እርቅ እንደሚፈልጉ ወደ ንጉሡ መልዕክት በላኩበት ጊዜ ነገሩ ያልተዋጠላት አዝማሪ ጣዲቄ …
“አውድማው ይለቅለቅ፤ በሮችም አይራቁ
ቀድሞም ያልኾነ ነው፤ ውትፍትፍ ነው እርቁ”
በማለት ጦር ሜዳውን በአውድማ፣ አርበኞችን በበሬ መስላ ገጥማለች።
የባሕል ጥናት ተመራማሪዋ አስቴር ሙሉ (ዶ.ር) ከዚህ በፊት ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት አዝማሪ በሰላም ጊዜ ያዝናናል፤ በጦርነት ጊዜ በፉከራ እና ቀረርቶ የዘማቹን የመዋጋት አቅም እንዲጠነክር አድርጓል፤ ጀብዱ የፈጸሙትን ይበልጥ አጀግነዋል።
በአድዋ ጦርነት የንጉሥ ሚካኤል አዝማሪ ሐሰን አማኑ እና የአጼ ምኒልክ አዝማሪ ጣዲቄን ጨምር በርካታ አዝማሪዎች ተሰልፈዋል።
ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት ወቅት፦
“ጣሊያን ገጠመ ከዳኘው ሙግት
አግቦ አስመሰለው በሠራው ጥይት” እያሉ ያነሳሱ ነበር።
በጦርነት ወቅት ጀግና ይቆስላል፤ ይሰዋል።
እነዚያን የተሰው ጀግኖችን
“ያ ትንታግ ተሰማ ምን አሉ ምን አሉ፣
እነ ደጃች ጫጫ ምን አሉ ምን አሉ፣ ተማምለው ነበር እጦሩ ሲገቡ፣
አልጋውን አቅንተው ዓድዋ ላይ ቀሩ”
“እንደሄደ ቀረ እንደገሰገሰ
የንጉሥ ባለሟል ቀኛዝማች ታደሰ”
“ያ በሻህ አቡዬ ያ ጎራው ገበየሁ ሁለቱም ያበዱ፣
እንቅር አይሉም ወይ አንዱ ሲሄድ አንዱ፣
በማለት የጀግኖችን ውለታ በጥበባቸው ታሪካቸውን ለትውልድ አስቀምጠው አልፈዋል።
“ሽሬ እንደሥላሴን ጠላት አረከሰው፣
ዓድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው፣
ገበየሁ ግባና በሞቴ ቀድሰው”
በማለትም አዚመዋል።
ጦርነቱ በኢትዮጵያውያን የበላይነት እንደተደመደመ
“አጨደው ከመረው ሰጠው ለነፋስ
የጊዮርጊስ ለት ሃብተ ጊዮርጊስ።
አሁን ማን አለ በዚህ ዓለም፣
ጣሊያን አስለቃሽ ቀን ሲጨልም” እየተባለ ይወደሳል።
“ባመጣው ወጨፎ በሠራው እርሳስ፣
ወቃው አመረተው ያንን የባሕር ገብስ፣
ዳኛው ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሥ”
“ዳኛው በዲሞቶር በለው በለው ሲል
የቃኘው መኮንን ደጀኑን አፍሶ ጦር ሲያደላድል፣
አባተ በመድፉ አምሳውን ሲገድል፣
ባልቻ በመትረይስ ነጥሎ ሲጥል፣
የጎጃሙ ንጉሥ በለው ግፋ ሲል፣
እቴጌ ጣይቱ ዳዊቷን ዘርግታ ስምዐኒ ስትል
ለቆለሰው ጀግና ውኃ ስታድል
እንዲህ ተሠርቶ ነው የዓድዋው ድል
እያሉ ያወድሱ ነበር።
የዓድዋ ጦርነት ጥቁሮችን ለጸረ ቅኝ አገዛዝ ያነሳሳ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሠረት የጣለ፣ የነጭ የበላይነትን ያከሰመ ነበር። የፋሽስቱን የኢጣሊያን መንግሥት ደግሞ በአጋጠመው ሽንፈት በሕዝቡ ከፍተኛ ውግዘት እና ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር። ሌሎች አውሮፓውያንንም ጭንቀት ውስጥ ጥሎ ነበር። ይህንንም
“ወዳጁም ሳቀ ጠላቱም ከሳ
ተንቀሳቀሰ ዳኛው ተነሳ
አራቱ አህጉር ለሱ እጅ ነሳ” ተብሎ ተወድሷል።
አዝማሪ ጣዲቄ በዓድዋ ጦርነት ላደረገችው አስተዋጽኦ ከምኒልክ እጅ ሽልማት እና የወይዘሮነት ማዕረግ እንዳገኘችም ይነገራል።
የጸሐፊ ታደሰ በቀለ ዳኘን ከቀዳማዊ እስከ ቀዳማዊ የሚለውን መጽሐፍ በተጨማሪ የመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!