
ፍኖተ ሰላም: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ”ቀበሌዎቻችንን በማጽናት ሁለንተናዊ እምርታን እናስመዘግባለን” በሚል መሪ መልዕክት የፍኖተ ሰላም ቀጣና ለቀበሌ መሪዎች በፍኖተ ሰላም ከተማ ሥልጠና እየተሰጠ ነው።
በሥልጠናው ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አማካሪ ባዬ አለባቸው በመሪዎች ቁርጠኝነት እና ትጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰላሙ ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል። አሁንም ማኅበረሰቡ ሙሉ በሙሉ የሰላም አየር እንዲተነፍስ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
መሪዎች በሥልጠና አቅምን በማጎልበት እና ከማኅበተሰብ ጋር በመቀናጀት ሰላምን መመለስ እንደሚገባቸው አንስተዋል።
አሁን ያለው የጸጥታ የማኅበረሰብ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች በተገቢው መንገድ ባለመፈታታቸው የመጣ ነው ብለዋል።
የቀበሌ መሪዎች ለማኅበረሰቡ ቅርብ በመኾናቸው ሥልጠናውን እንደ ግብዓት በመውሰድ ለልማት እና ለሰላም መትጋት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ እድሜዓለም አንተነህ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ራስን በራስ የማጥፋት ተግባር መኾኑን ገልጸዋል። በተለይም የተፈጠረውን ሁለንተናዊ ቀውስ ለመቀልበስ መሪዎች ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል ።
የሚሰጠውን ሥልጠና በመጠቀም እና ሰላሙን በመመለስ ወደ ልማት ለመዞር የቀበሌ መሪዎች ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው ነው ያሉት።
በምዕራብ ጎጃም ዞን ለተከታታይ ሦስት ቀናት የሚሰጠው የቀበሌ መሪዎች ሥልጠና ፍኖተ ሰላም፣ ደንበጫ እና ቡሬ ቀጣናዎች እየተሰጠ ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!