
ሁመራ: የካቲት 22/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሰላም፣ ልማት፣ ሕግ እና ሥርዓት መረጋገጡን ባለፉት ሰባት ወራት በዞኑ የተከናወኑ አፈጻጸሞች ግምገማ እና የቀሪ ወራት ማስፈጸሚያ እቅድ ትውውቅ መድረክ ላይ ተገልጿል።
ክልላችን የገጠመው የጸጥታ ችግር ዞኑንም ገጥሞት ነበር ያሉት የመድረኩ ተሳታፊዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዞኑን ሰላም ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
የሰላም ጉዳይ በውይይቱ ጎልቶ የተነሳ ትልቅ አጀንዳ ነበር ያሉት ተሳታፊዎቹ ዛሬ ከሰላም እና ከጸጥታ ሥራዎች ወጥተን ፊታችንን ወደ ልማት ማዞራችን በመልካም ጎን የተገመገመ አፈጻጸ ኾናል ብለዋል።
የሕዝቡን የአገልግሎት ፍላጎት ለማርካት ብቁ አመራር እና ጠንካራ ተቋም እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል ያሉት ተሳታፊዎቹ በእውቀት እና በአመለካከት የታነጸ አመራር መፍጠር ከቀጣይ አቅጣጫዎች መካከል የሚጠቀስ መኾኑን ተናግረዋል።
አካባቢው ከዚህ በፊት በነበረው ጦርነት ብዙ መሠረተ ልማቱ የወደመበት በመኾኑ በጦርነቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው ሌሎች የክልሉ አካባቢዎች ሁሉ ዞናችንም በጀት ተበጅቶለት መልሶ ግንባታ ሊደረግ ይገባል የሚል ጥያቄም ከተሳታፊዎች ተነስቷል።
የግብር ገቢን በአግባቡ አለመሰብሰብ፣ ራስን ለተቀመጡለት የሥራ መደብ አለማብቃት፣ የፌደራል ተቋማት በዞኑ በአግባቡ ሥራቸውን አለመሥራት ወደፊት ሊስተካከሉ ይገባቸዋል ተብለው የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።
በዞኑ ሰላም፣ ልማት፣ ሕግ እና ሥርዓት እንዲረጋገጥ መሠራቱን ገምግመናል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኀላፊ ሲሳይ ዳምጤ ናቸው። ዛሬ ላይ ዞኑ ሰላም ከተረጋገጠባቸው የሀገራችን አካባቢዎች መካከል አንዱ መኾኑንም አቶ ሲሳይ ጠቅሰዋል።
ይህ የኾነው ግን በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች የገጠመን የጸጥታ መደፍረስ በዚህም ዞን ሳይፈጠር ቀርቶ ሳይኾን የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልሉ መንግሥት እና የዞኑ አመራር እና የጸጥታ መዋቅር በጥምረት በሠሩት ሥራ ነው ብለዋል።
በመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ ሲሳይ የመሠረተ ልማት ግንባታን፣ መልሶ ግንባታን እና ሌሎች ጥያቄዎችን ለመመለስ የክልሉ መንግሥት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝቶ ለመሥራት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል።
ሕዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ሠርቶ ማግኘት እና ነግዶ ማትረፍ የሚችልበትን የሰላም ሁኔታ ፈጥረናል ያሉት ደግሞ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረ እግዚአብሔር ደሴ ናቸው።
ባለፉት ሰባት ወራት ያሳካናቸው ሥራዎች ሳያኩራሩን በጉድለት የተመለከትናቸውን ጉዳዮች በቀሪ ወራት ለማሻሻል እና ለመሥራት እድል ያገኘንበት መድረክ ነው ሲሉ ኀላፊው ጠቁመዋል።
ብቁ አመራር እና ጠንካራ መዋቅር መፍጠር ልንሠራባቸው ከሚገቡን የቤት ሥራዎች መካከል ናቸው ሲሉም አቶ ገብረ እግዚአብሔር ጠቅሰዋል።
ሕዝቡ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸው የልማት ጥያቄዎች በተለይም የኤርፖርቱ ወደ አገልግሎት አለመግባት፣ የመብራት ኃይል በሙሉ አቅሙ ሥራ አለመጀመር እና ሌሎች ጉዳዮች የሕዝብን የአገልግሎት እርካታ የሚቀንሱ ስለኾኑ የበኩላችንን ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን