
ጎንደር: የካቲት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳደር በዞኑ ጽሕፈት ቤት ሥር የሚገኙ መዛግብትን እና ሰነዶችን ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለማዘዋወር፤ ለመጠበቅ እና ለማልማት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል። ታሪካዊ ሰነዶቹ ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሚቀመጡበት ጉዳይ ከዞኑ የሥራ ኀላፊዎች፤ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥራ ኀላፊዎች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይትም ተካሂዷል።
የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አሥተዳዳሪ አወቀ አስፈሬ አሁን ለደረስንበት ዘመን የበፊት ታሪኮች ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል። ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማስረከብ አስፈልጓል ብለዋል። ሰነዶቹ በቀድሞው ሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛት እና በቀድሞው ሰሜን ጎንደር ዞን የነበሩ ታሪካዊ ሰነዶች መኾናቸውንም ገልጸዋል።
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ረዳት አገኘሁ ተስፋ (ዶ.ር) ትናንትን ለመረዳት እና የዛሬን ለመሥራት ሰነዶቹ የትውልድ ቅብብሎሽን ለመፍጠር የሚያግዙ መኾናቸውን አንስተዋል። ታሪካዊ ሰነዶቹ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ተማሪዎች ለምርምር እንዲጠቀሙበት የሚያግዝ መኾኑን ተናግረዋል። ሰነዶቹ በአግባብ ባለመያዛቸው ጉዳት ይደርስባቸው እንደነበር አንስተዋል። ዩኒቨርሲቲው ቦታ በማዘጋጀት ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲቀመጥ ለማድረግ እንደሠራም አንስተዋል።
በቀጣይ በቴክኖሎጅ በማዘመን ሰነዶቹ በኮምፒውተርም እንዲቀመጡ እንደሚሠራም ተናግረዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ታሪካዊ ሰነዶቹ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ መቀመጣቸው የአካባቢውን ባሕል እና ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚያግዙ ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችም ከሰነዶቹ በማጣቀስ የሰሜን በጌምድር ጠቅላይ ግዛትን ታሪክ የሚያውቁበት እና ለጥናትና ምርምር የሚያግዝ መኾኑን ተናግረዋል። በቀጣይ ተግባራት ሰነዶቹን ወደ ዩኒቨርሲቲው የማዘዋወር ሥራ እንደሚከናወንም በውይይቱ ተገልጿል።
ዘጋቢ: ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!