“አንድነታችንን በማጠናከር እና የወል ትርክትን በመገንባት የዘመኑ አርበኛ ልንኾን ይገባል” አየለ አናውጤ (ዶ.ር)

41

ጎንደር: የካቲት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በማዕከላዊ ጎንደር ዞን “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት” በሚል መሪ መልዕክት ተከብሯል። በዞኑ ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ በተዘጋጀው የዝክረ ዓድዋ መርሐ ግብር የአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳድሩ የኢኮኖሚ አማካሪ ቀለም ወርቅ ምህረቴ፣ የአማራ ክልል የባሕል እና ቱሪዝም ምክትል ቢሮ ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር)፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሥራ ኀላፊዎች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መሪዎች፣ አርበኞች እና የመንግሥት ሠራተኞች ተሳታፊ ኾነዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አቤል መብት የዓድዋ ድል የዓለምን ታሪክ የቀየረ፤ አዲስ እሳቤን የፈጠረ እና የኢትዮጵያን ከፍታ ያሳየ ድንቅ ታሪክ ነው ብለዋል። ዓድዋ ለአሁኑ ሀገራዊ ሰላም መሠረት መኾኑን ተናግረዋል። ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማስጠበቅ፤ የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር፤ ጀግንነት እና ቆራጥነትን ያስተማረ ድል እንደኾነም አንስተዋል።

የአማራ ክልል የባሕል እና ቱሪዝም ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በአንድነት ለሀገራቸው ለሉዓላዊነት የወደቁ አባቶች እና እናቶችን ታሪክ ከመዘከር ባሻገር አንድነትን በማጠናከር እና ድህነትን በመዋጋት የሀገርን ታሪክ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
መስለን ሳይኾን በተግባር የዚህ ዘመን አርበኛ መኾን ይገባል ነው ያሉት።

አፍሪካዊያን በየዓመቱ ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡበትን የነጻነት በዓል ሲያከብሩ እኛ ግን የነጻነት የድል ታሪክን እናከብራለን ብለዋል። ዓድዋን ስናከብር ከከፋፋይ ነጠላ ትርክት ይልቅ አካታች ትርክትን በመፍጠር የዚህ ዘመን አርበኛ መኾን ይገባል ነው ያሉት። “አንድነታችንን በማጠናከር እና የወል ትርክትን በመገንባት የዘመኑ አርበኛ ልንኾን ይገባል” ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ የሰሜን ጎንደር ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ዋና ጽሐፊ መስፍን አያሌው የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ነው ብለዋል። ጥቁር ሕዝቦች ማሸነፍ እንደሚችሉ ያሳዩበት ብሔራዊ የድል በዓል እንደኾነም አብራርተዋል። የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን ታሪክ በመጠበቅ የሀገሩን ሉዓላዊነት ሊያስጠብቅ ይገባልም ብለዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የሥነ ልቦና ግንባታ ኀላፊ ኮሎኔል ተስፋየ ኤፍሬም የዓድዋን ታሪክ በማስቀጠል እና ለቀጣይ ትውልድ በማስተላለፍ የሀገርን አንድነት ማስጠበቅ ይገባል ነው ያሉት። ዘር ቀለም ሃይማኖት እንደማይለየን ከዓድዋ ታሪክ በመማር ለአንድነት በተግባር ልንሠራ ይገባልም ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበጫካ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።
Next articleየማዕከላዊ ጎንደር ዞን እና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ታሪካዊ ሰነዶችን ለመረካከብ ተስማሙ።