የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በኑሯቸው ላይ ለውጥ እንዲመጣ ማድረጉን አርሶ አደሮች ተናገሩ።

22

ጎንደር: የካቲት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ከተማ አሥተዳደር ፈንጠር ቀበሌ 40 አርሶ አደሮች በክላስተር በ10 ሔክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ስንዴ እያለሙ ነው። የከተማ አሥተዳደሩ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የግብርና መምሪያ ሠራተኞች እና አርሶ አደሮች የተሳተፉበት የድጋፍ እና የክትትል ጉብኝት በዚሁ ቀበሌ ተካሂዷል።

በጉብኝቱ አርሶ አደሮቹ የበጋ መስኖ ስንዴ በማልማታቸው በኑሯቸው ላይ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።የግብዓት እጥረት መኖሩን የተናገሩት አርሶ አደሮቹ መፍትሔ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል። የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ ተወካይ ኀላፊ በየነ ሙጨ ጉብኝቱ የልምድ ልውውጥ መድረክ ኾኖ ያገለግላል ብለዋል።

የጎንደር ከተማ ምክር ቤት የኢኮኖሚ ልማት፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ አያናው ተገኘ የልማት ሥራው በበጀት እየተደገፈ እንደሚሠራ ገልጸዋል። በአጠቃላይ 574 ሄክታር መሬት ላይ የበጋ መስኖ ሥራ መከናወኑን መመልከታቸውን አስረድተዋል። በበጋ መስኖ ሥራው ላይ 1 ሺህ 100 በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ መኾኑን ገልጸዋል። የግብዓት ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።

የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ግብርና መምሪያ 1 ሺህ 300 ሄክታር የሚጠጋ መሬት በሦስተኛ ዙር የመስኖ ሥራ ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን አስታውቋል።

ዘጋቢ፦ ዳንኤል ወርቄ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዓድዋ የነጮችን የተሳሳተ አስተሳሰብ በተግባር ውድቅ ያደረገ ድል ነው” የታሪክ መምህሩ አሸናፊ ገብረ ጻድቅ
Next articleበጫካ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀበሉ።