
ደብረ ብርሃን: የካቲት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ጉዳይ ተለያይተው አያውቁም። ቅኝ ያለመገዛታቸው ምስጢር ይሄ ነው። ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የታሪክ መምህሩ አሸናፊ ገብረ ጻድቅ ዓድዋ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለ ዘር፣ ያለ ቋንቋ እና ያለ ሃይማኖት ልዩነት በአንድነት ዘምተው በአንድነት ደማቅ ድልን የተቀዳጁበት ነው ይላሉ።
“ዓድዋ የነጮችን የበላይ ነን የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ በተግባር ውድቅ ያደረገ ድል ነው” ብለዋል። አሚኮ ያነጋገራቸው በደብረ ብርሃን ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኩራት መኾኑን ገልጸዋል። በዓለም ላይ የሚገኙ የጥቁር ሕዝቦችን ሁሉ ለነጻነት ትግል ያስነሳ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ነውም ብለዋል። ዓድዋን በልኩ በመዘከር ትውልዱ ስለቅድመ አያቶቹ ጀግንነት እና ሀገር ወዳድነት በተገቢው እንዲገነዘብ እና የራሱን ታሪክ እንዲሠራ በማድረግ ረገድ በቂ ተግባራት አለመሠራታቸውን አንስተዋል።
መገናኛ ብዙሃን፣ የትምህርት ተቋማት እና የታሪክ ምሁራን ስለ ዓድዋ ለትውልዱ በስፋት የማሳወቅ እና የማስገንዘብ ኀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል።
ዘጋቢ: ሥነ ጊዮርጊስ ከበደ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!