
ባሕር ዳር: የካቲት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ ባለፉት ሦስት ዓመታት በሀገሪቱ የሳይበር ደኅንነትን የማስጠበቅ አቅም መሻሻሉን ገልጸዋል። ዳይሬክተሯ ለብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ተቋሙ የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲዎችን በማሻሻል፣ የሰው ኀይል በማሠልጠን እና የቴክኖሎጂ አቅምን በማጠናከር አደጋዎችን መከላከል የሚችል ማዕከል ገንብቷል ብለዋል።
በተጨማሪም ከዓለም ሀገራት ጋር በመተባበር መረጃን በመለዋወጥ እና የቴክኖሎጂ ቁጥጥርን በማጠናከር እየሠራ መኾኑን ጠቁመዋል። የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እና ተቋማት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ሥልጠናዎች እየተሰጡ መኾኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ በሳይበር ደኅንነት ላይ ትኩረት ያደረገ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት እየተሠራ ነው ብለዋል።
ኢመደአ ኮምፒውተርን መሠረት ያደረጉ ማንኛውም አይነት የወንጀል ድርጊቶች ለሚመለከተው የፍትሕ አካላት የማቅረብ እንዲሁም ለሀገር ደኅንነት ስጋት የኾኑ የቴክኖሎጂ እቃዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ተጋላጭነታቸውን የመፈተሽ እና ፍቃድ የመስጠት ሥራ በቴክኖሎጂ ቁጥጥር እያከናወነ መኾኑንም ዳይሬክተሯ መግለጻቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አሥተዳደር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!