
እንጅባራ: የካቲት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ መልዕክት በፓርቲው 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በተቀመጡ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከአባላት እና ደጋፊዎች ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ላስመዘገባቸው ስኬቶች የሴቶች ድርሻ የጎላ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በተለይም በክልሉ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለማርገብ ሴቶች ትልቅ ሚና እንደተጫወቱም አንስተዋል፡፡
ሴቶች ለሀገር ግንባታ ያላቸው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ አቅማቸውን ማጎልበት የብልጽግና ፓርቲ አንዱ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መኾኑን ዋና አሥተዳዳሪው አሳስበዋል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሴቶች ክንፍ ኀላፊ ከበቡሽ ፈለቀ ብልጽግና በተመሠረተ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጨባጭ ለውጦችን ያስመዘገበ ፓርቲ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ሀገር የሚገነባው በተገነባ ትውልድ ነው ያሉት ኀላፊዋ ለዚህ ደግሞ የሴቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ፓርቲው በ2ኛ መደበኛ ጉባኤው የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች በተግባር ለማዋል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፦ ሳሙኤል አማረ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!