“ባሕልን በበጎ እና በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለመንፈስ መታደስ እና ለአብሮነት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው” ከንቲባ አዳነች አቤቤ

31

አዲስ አበባ: የካቲት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ለተከታታይ ሦስት ቀናት በተለያዩ የባሕል ዝግጅቶች የሚከወነው 16ኛው ከተማ አቀፍ የባሕል ፌስቲቫል በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና የግል ተቋማት ኀላፊዎች በተገኙበት በግዮን ሆቴል ተከፍቷል።

ፌስቲቫሉ “ባሕሎቻችን የወል ትርክት አምባ” በሚል መሪ መልዕክት በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የባሕል ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የተዘጋጀ ነው። ፌስቲቫሉን ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያ የብዙ ባሕል ባለጸጋ መኾኗን ጠቅሰዋል። “ባሕልን በበጎ እና በአግባቡ ከተጠቀምንበት ለመንፈስ መታደስ እና ለአብሮነት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው” ነው ያሉት።

የሌላን ባሕል ከመከተል እና ከመተግበር ይልቅ ኢትዮጵያን የሚገልጹ ብዙ ባሕሎችን በማሳደግ ከተጠቀምንባቸው ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል። ፌስቲቫሉ መከፈቱ የተለያዩ ባሕሎችን የሚያሳይ በመኾኑ ሁሉም ባሕሉን እንዲያውቅ እና ባሕል የበጎነት መገለጫ መኾኑን እንዲገነዘብ ያደርጋል ነው ያሉት።

መንግሥትም ለባሕሎች ከፍተኛ ክትትል በማድረግ ባሕሎች በጎ ተግባራትን እንዲያመጡ እና የአሁኑ ትውልድ ያለፈውን ድንቅ እና መልካም ባሕሉን እንዲከተል ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል። በፌስቲቫሉ የኢትዮጵያ የባሕል አልባሳት፣ የአመጋገብ ሥርዓት፣ የአኗኗር ዘይቤ እና የጭፈራ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

ዘጋቢ፦ ራሄል ደምሰው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዓድዋ የጽናት፣ የአንድነት እና የሀገር ኩራት ነው” የአሜሪካ ኤምባሲ
Next article“ሴቶች ለሀገር ግንባታ ያላቸው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅማቸውን ማጎልበት ማስቻል የትኩረት አቅጣጫ ነው” የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር