ትላንት አባቶች በደም እና በአጥንታቸው ያጸኗትን ሀገር ወጣቱ ትውልድ ሊጠብቃት ይገባል።

31

ሰቆጣ: የካቲት 21/2017 ዓ.ም (አሚኮ)ለአፍሪካ የነጻነት ችቦ የለኮሰው ፣ለጥቁር ሕዝቦች የይቻላል ወኔን የሰጠ ነው የዓድዋ ድል ። የዓድዋን ድል ለማግኘትም ኢትዮጵያን ዘር ፣ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለዩ በአንድነት ተዋድቀው የእናት ሀገርን ባንዴራ ከፍ አድርገዋል። በሰቆጣ ከተማ የወጣቶች ማኅበር አባላት ለዓድዋ ድል በዓል የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓት አካሂደዋል።

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት ጽዮን ደሴ የዓድዋ ድል ሲታወስ የእቴጌ ጣይቱ የመሪነት ብቃት አብሮ እንደሚታወስ ተናግራለች። አባቶች እና እናቶች በእኩልነት ዘምተው ለአፍሪካ የሚበቃ ድል ትተው ማለፋቸውን ነው የገለጸችው። ወጣት ሴቶችም ለሀገራቸው ሰላም እንደ እቴጌ ጣይቱ ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግራለች።

የሰቆጣ ከተማ አባት አርበኞች አባል ምክትል ኮማንደር ሹሜ ንጉሤ ትላንት አባቶች በደም እና በአጥንታቸው ያጸኗትን ሀገር ወጣቱ ትውልድ ሊጠብቃት እንደሚገባ ገልጸዋል። ፋሽስት የኢትዮጵያውያን መለያየትን እንደ መልካም ዕድል ተጠቅሞ ሀገርን ለመውረር በመጣ ጊዜ የውስጥ ችግር በውይይት ይፈታል በሚል ጠብቀው ማቆየታቸውን ተናግረዋል።

ዛሬም ትውልዱ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ከእርስ በእርስ ግጭት ወጥቶ ሀገሩን ከተጋረጠባት አደጋ ማውጣት ይገባዋል ነው ያሉት። የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ማኅበር ሠብሣቢ ወጣት ወንድሙ በላይ የዓድዋ ድል ለአፍሪካ የነጻነት ችቦ የለኮሰ፣ ለጥቁር ሕዝቦች የይቻላል ወኔን የሰጠ ታላቅ ድል ነው ብሏል።

ዓድዋ ላይ ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ቀለም፣ ሃይማኖት ሳይለዩ በአንድነት ተዋድቀው የእናት ሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገዋል ነው ያለው። በዓድዋ ድል የተገኘውን ነጻነት በመጠቀም የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር መዘጋጀታቸውን ገልጿል። የሰቆጣ ወጣቶች የአካባቢውን ሰላም ለማጽናት በአደረጃጀት ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመቆም እየሠሩ እንደኾነም ተናግሯል።

የሰቆጣ ከተማ ወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ሠብሣቢ ወጣት ደስታ አወጣ ልዩነትን በውይይት መፍታት የሠለጠነ ትውልድ መገለጫ መኾኑን ገልጻለች። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከገጠመው የእርስ በእርስ ግጭት በመውጣት እንደ ዓድዋው ድል ዓለምን ያስደመመ የልማት ድል ማስመዝገብ እንደሚቻል ተናግራለች።
ዓድዋ ኢትዮጵያዊያንን አንድነታቸውን ለዓለም ያሳዩበት የድል መኾኑን ወጣቶቹ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ደጀን ታምሩ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዓድዋ አባቶች በመስዋዕትነት ያቆዩት ታሪክ የማይሽረው ስጦታ ነው።
Next articleተላላፊ ስላልኾኑ በሽታዎች ምን ያህል ያውቃሉ?