ለአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች ማዘጋጀቱን የምዕራብ ጎጃም ዞን ገለጸ።

27

ፍኖተ ሰላም: የካቲት 20/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ለ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የቅድመ ዝግጅት ተግባራትን እያከናወነ ነው። በጃቢ ጠህናን ወረዳ አራራ ችግኝ ጣቢያ የሙዝ፣ ፓፓዬ፣ ቡና እና አቮካዶ ዝርያዎችን በማሻሻል ለአካባቢው አርሶ አደሮች እያደረሰ ነው። በዚህ ዓመት ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የአትክልት እና ፍራፍሬ በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች ለማድረስ እየተሠራ ይገኛል።

በአራራ ችግኝ ጣቢያ የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያ እና የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ወይዘሮ አለሚቱ አደመ የችግኞችን ዝርያ በማሻሻል ለተጠቃሚዎች እያደረሱ መኾኑን ተናግረዋል። የአራራ ችግኝ ጣቢያ ተቆጣጣሪ ዳንኤል ሙሉጌታ በዚህ ዓመት እስከ 500ሺህ የሚጠጉ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። ከችግኝ ልማቱ ባለፈ ለ56 ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረጉንም ተናግረዋል።

በቡሬ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት የአትክልት እና ፍራፍሬ ቡድን መሪ መንግሥቱ ደሴ በወረዳው በሁለት የመንግሥት እና በ19 የአርሶ አደር ጣቢያዎች ለ2017 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከ153ሺህ በላይ የአትክልት እና ፍራፍሬ ችግኞች በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች ለማድረስ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በርካታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መኾን መቻላቸውንም ተናግረዋል። የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ተስፋዬ አስማረ በዚህ ዓመት ለሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል። በ168 የግል፣ የማኅበር እና የአርሶ አደር የችግኝ ጣቢያዎች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሙዝ፣ አቮካዶ፣ ቡና፣ ፓፓዬ እና ማንጎ መዘጋጀቱን አመላክተዋል።

አርሶ አደሮች በአትክልት እና ፍራፍሬ ተጠቃሚ በመኾናቸው ልዩ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ነው ብለዋል። የአትክልት እና ፍራፍሬ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ ለባለሙያዎች በዝርያ ማሻሻል ዙሪያ ሥልጠና መሰጠቱንም አንስተዋል።

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleባዮሜትሪክ የደኅንነት ሥርዓት
Next articleየአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጀመረው መሠረታዊ የተቋም ለውጥ ፈጣን፣ ዘላቂ እና ውጤታማ እንዲኾን ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቀረበ።